ሳዑዲ አረቢያ በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የአልኮል መሸጫ መደብር ልትከፍት ነው
በሪያድ የሚከፈተው የአልኮል መሸጫ ሙስሊም ያልሆኑ ዲፕሎማቶችን ብቻ ያገለግላል
ሳዑዲ አረቢያ አልኮልን መጠጣትን የሚከለክል ጥብቅና ከባድ ቅጣት የሚያስከትል ህጎች አላት
ሳዑዲ አረቢያ በሀገሪቱ መጀመሪያ የሆነውን የአልኮል መሸጫ መደብር በዋና ከተማዋ ሪያድ ለመክፈት በዝግጅት ላይ መሆኗ ተገለጸ።
በሪያድ የሚከፈተው የአልኮል መሸጫ መደብር ሙስሊም ያልሆኑ ዲፕሎማቶችን ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ሮይተርስ የውስጥ አዋቂ ምንጮችን እና ሰነዶችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ተጠቃሚዎች በሞባይል ስልካቸው በመመዝገብ ከሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የማረጋገጫ ቁጥር ካገኙ በኋላ አልኮል መግዛት የሚችሉ ሲሆን፤ ለተጠቃሚዎችም ውሃዊ ኮታ መዘጋጀቱንም ሰነዱ ያመላክታል።
እርምጃው አልኮል መጠጣት በጥብቅ የተከለከለ በሆነባት ወግ አጥባቂ ሙስሊም ሀገር የሆነችው ሳዑዲ አረቢያ በሯን ለቱሪዝም እና ለንግድ ስራ ለመክፈት በምታደርገው ጥረት ትልቅ ምዕራፍ ነው ተብሏል።
በተጨማሪም የድህረ ነዳጅ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሳዑዲ አረቢያ ያስቀመጠችው እና ራዕይ 2030 በመባል የሚታወቀው የሰፋፊ ዕቅዶች አካል እንደሆነም ተመላክቷል።
በዚሁ መሰረት አዲሱ የመጠጥ መሸጫ መደብር የሚገኘው ኤምባሲዎች በሚገኙበት እና ዲፕሎማቶች በሚኖሩበት ዲፕሎማቲክ ሰፈር ውስጥ ነው ይላል ሰነዱ።
ከዲፕሎማቶች ውጪ ሌሎች ሙስሊም ያለሆኑ እና በሀገሪቱ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ አልኮል መሸጫው ጎራ ብለው አልኮል መግዛት ይችሉ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
ስለ እቅዶቹ የሚያውቅ የውስጥ ምንጭ እንዳስታወቀው የአልኮል መሸጫ ሱቁ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ሊከፈት ይችላል።
ሳዑዲ አረቢያ አልኮልን መጠጣት የሚከለክል ጥብቅ ህግ ያላት ሲሆን፤ በአሀሪቱ አለኮል ይዞ የተገኘ ሰው በመቶዎች የሚቆጠሩ ግርፊያ፣ እስር እና ከሀገር እስከ መባረር የሚደረስ ቅጣቶች ይጠብቁታል።
በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ አልኮል ማግኘት የሚቻለውም በዲፕሎማቲክ ልዩ መልእክቶች ወይም በጥቁር ገበያ ብቻ እንደሆነም ይታወቃል።