ሜዲትራኒያን ባህር ላይ የሰጠሙ አፍሪካውያን ስደተኞች ቁጥር 39 ደረሰ
የቱኒዝያ ብሔራዊ ዘብ 165 ያህሉን ተጓዦች በህይወት ለመታደግ ስለመቻሉም ነው የተገለጸው
ስደተኞቹ ባህሩን አቋርጠው ወደ ጣልያን ላምፔዱሳ ያመሩ ነበር ተብሏል
ስደተኞች በጣልያኗ ላምፔዱሳ ደሴት በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር በማሰብ በሁለት አነስተኛ መጓጓዣ መርከቦች አማካኝነት ሲጓዙ ነበር በሜድትራኒያን ባህር ላይ አደጋ የደረሰባቸው።
በዚህ የመስጠም አደጋ ምክንያትም አራት ህጻናትን ጨምሮ በትንሹ 39 ስደተኞች ሲሞቱ 165 ያህሉ ደግሞ የቱኒዝያ ብሔራዊ ዘብ እንደታደጋቸው ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ይሁንና ወደ በጣልያን አድርገው ወደ አውሮፓ ከተሞች ለመግብት በመርከቦቹ ምን ያህል ስደተኞች ጉዞ አንደጀመሩ እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን ተጨማሪ የሞቱ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል አስከሬን ፍለጋው እንደቀጠለ ዘገባው ጠቁሟል።
የቱኒዝያ ባለስልጣናት እንደተናገሩት በአደገኛ ሁኔታ ወደ አውሮፓ በመጓዝ ላይ እያሉ የመስጠም አደጋ የደረሰባቸው እነዚህ ስደተኞች ሁሉም ከሰብ ሰሃራ የአፍሪካ አገራት የመጡ ናቸው።
ባሳለፍነው ሳምንት ከ20 በላይ ስደተኞች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመግባት በሚል ጉዞ የጀመሩ ስደተኞች ጅቡቲ ላይ በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ተገፍትረው እንዲሰጥሙ እና እንዲሞቱ መደረጉን የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል።
የቱኒዝያ ባህረኞች ባለፉት 12 ወራት ከ13 ሺህ በላይ ወደ አውሮፓ በህገ ወጥ መንገድ ለመጓዝ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ የገባ ስደተኞችን እንደታደጉ ዘገባው ጠቁሟል።