በታይላንድ በመዋለ ሕጻናት ማእከል ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 34 ሰዎች ተገደሉ
በጥቃቱ ከተገደሉት መካከል 22 ቱ ህጻናት ናቸው

ግድያውን የፈጸመው የቀድሞ ፖሊስ አባል የነበረ መሆኑ ተገልጿል
በታይላንድ ሐሙስ ዕለት 34 ሰዎች በአንድ የመዋለ ሕጻናት ማቆያ ውስጥ በጅምላ ተኩስ ተገደሉ።
ግድያውን የፈጸመው የቀድሞ ፖሊስ ራሱን ተኩሶ ከመግደሉ በፊት ሚስቱንና ልጁን መግደሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
በታጣቂው ግለሰብ ከተገደሉት መካከል 22 ህጻናት የሚገኙበት ሲሆን ተጠርጣሪው ታጣቂ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተገናኘ ከአገልግሎት መውጣቱ ተነግሯል።
ታጣቂው ጥቃ በከፈተበት ምሳ ሰአት አካባቢ ወደ 30 የሚጠጉ ህጻናት በማዕከሉ ውስጥ እንደነበሩ የዲስትሪክቱ ባለስልጣን ጂዳፓ ቦንሶም ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ሰውየው በመጀመሪያ የስምንት ወር ነፍሰ ጡር የሆነችውን አስተማሪን ጨምሮ አራት ወይም አምስት ሰራተኞችን በጥይት መግደሉን ጂዳፓ ገልጸዋል።
ጂዳፖ አክለውም “መጀመሪያ ላይ ሰዎች ርችት እንደሆነ አድርገው ያስቡ" ነበር ብለዋል።
በሰሜን ምስራቅ ኖንግ ቡዋ ላምፑ ግዛት ውስጥ በኡታይ ሳዋን ከተማ መሃል ላይ በደም ገንዳ ውስጥ የተኙትን የህፃናት አስከሬን በአንሶላ ሲሸፈን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፉ ቪዲዮዎች ያሳያሉ።
ሮይተርስ የቪዲዮውን ትክክለኛነት ወዲያውኑ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።
ቀደም ሲል ፖሊስ ተኳሹን ለመያዝ አደን እየተካሄደ መሆኑን የገለፀ ሲሆን የመንግስት ቃል አቀባይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጀለኛውን ለመያዝ ሁሉንም ኤጀንሲዎች ማሳወቃቸውን ተናግሯል።
በታይላንድ ውስጥ የጅምላ ተኩስ ብዙም ያልተለመደ ነው። ምንም እንኳን በክልሉ ውስጥ ካሉ አንዳንድ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የጠመንጃ ባለቤትነት መጠኑ ከፍተኛ ቢሆንም ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች የተለመዱ ናቸው።