አውሮፓ ህብረት የዩክሬን ግዛቶችን በጠቀለለችው ሩሲያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች ለመጣል መስማማቱ አስታወቀ
አውሮፓ ህብርት በሞስኮ ላይ ማዕቀብ ሲጥል ይህ ለስምንተኛ ጊዜ መሆኑ ነው
በህብረቱ የቼክ ተወካይ አምባሳደር እዲታ ህርዳ “ለፑቲን ህገ-ወጥ የግዛት ይዞታ ጠንካራ ምላሽ እንሰጣለን” ብለዋል
አውሮፓ ህብረት፤ የዩክሬን አራት ግዛቶችን በጠቀለለችው ሩሲያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች ለመጣል መስማማቱ የወቅቱ የህብረቱ ምክር ቤት ሊቀ መንበር ቼክ ሪፐብሊክ አስታወቀች፡፡
በአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት የቼክ ሪፐብሊክ ተወካይ አምባሳደር እዲታ ህርዳ በትዊትተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ፤ ማዕቀቦቹ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ ስምንተኛ ሲሆን ካለምንም ተቃውሞ ከጸደቀ ታትሞ ሐሙስ ላይ ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡
"በሩሲያ ላይ በሚጣሉ አዳዲስ ማዕቀቦች ላይ የፖለቲካ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ለፑቲን ህገ-ወጥ የግዛት ይዞታ ጠንካራ የአውሮፓ ህብረት ምላሽ እንሰጣለን"ም ነው ያሉት አምባሳደሯ፡፡
አምባሳደሯ በማዕቀቦቹ ዝርዝር ላይ ያሉት ነገር ባይኖርም የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮች ባለፉት ጥቂት ቀናት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎችን ሲወያዩ እንደነበር ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ከማዕቀቦቹ በዓለም ዙሪያ በሚጓጓዘው የሩስያ ዘይት ላይ የዋጋ ገደብ መጣል አንዱ ሊሆን እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ጦርነት እስከቀጠለችበት ህብረቱ በክሬምሊን ላይ የሚጥለው ማዕቀብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እንዲሁም የተጣለው ማዕቀብ እስከ ጥር 2023 እንዲራዘም ከውሳኔ መደረሱ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ “ሞስኮ ለጥቃቱ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን መቀጠል አለባት” ብለውም ነበር፡፡
አውሮፓውያን ይህን ይበሉ እንጂ ፤ የምዕራባውያን ማዕቀቦች እያዘነቡባት ያለችው ሩሲያ “ዓላማዬን እስካሳካ ድረስ የሚቆም ወታደራዊ ዘመቻ የለም” ስትል እየተደመጠች ነው፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከሁለት ሳምንታት በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው መጀመሪያ ላይ የተቀመጡት አላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል" ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡