ታይላንድ የካናቢስ ዕጽ ንግድ ህጋዊ አደረገች
የታይላንድ መንግስት የካናቢስ ንግድ ቢፈቀድም “እጽ እንደ መዝናኛ መጠቀም” ክልክል ነው ብሏል
አንድ የታይላንድ ቤተሰብ እስከ ስድስት የካናቢስ ዘር በቤቱ ሊያመርት ይችላል ተብሏል
ታይላንድ ዜጎቿ በህጋዊ መንገድ ካናቢስ እንዲያመርቱና እንዲሸጡ የሚያስችል የህግ ማሻሻያ ማድርጓ ይፋ አደረገች፡፡
ታይላንድ ይህንን ማሻሻያ ስታደረግ ጠንካራ የሚባል የእጽ ህግ ባለበት ደቡብ ምስራቅ እስያ አከባቢ ከሚገኙ ሀገራት ቀዳሚዋ ናት፡፡
ይሁን እንጅ እጽ እንደ መዝናኛ መጠቀምና በየአደባባዩ ማጨስ አሁንም ክልክል መሆኑ የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡
ካናቢስ ለመዝናኛነት ሲጠቀም የተገኘ ማንኛውም ሰው “የሶስት ወራት እስራት እና 780 ዶላር ቅጣት ይጠብቀዋል”ም ነው ያለው የሀገሪቱ መንግስት፡፡የሀገሪቱ መንግስት ማሻሻያ ያደረገበት ምክንያት “የካናቢስ ንግድ ማሳደግ የሀገሪቱን የግብርና እና ቱሪዝም ዘርፍ ለማጠናከር “በሚል መሆኑ ገልጿል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሀገሪቱ መንግስት የካናቢስ ምርትን ለማበረታታት አንድ ሚሊዮን የካናቢስ ዘር አዘጋጅቶ አምራቾች በነጻ እንዲወስዱ እያደረገ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
በዚህም አንድ የታይላንድ ቤተሰብ እስከ ስድስት ካናቢስ በቤቱ ሊያመርት ይችላል ተብሏል፡፡
ፍቃድ የሰተጣቸው ተቋማትም እንዲሁ ካናቢስ ሊያመርቱ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡የምግብ ቤት ደምበኞች በሆቴሎች በካናቢስ የተዘጋጁ ምግቦችና መጠጦች ሊያዙ ይችላሉም ነው የተባለው፡፡
አሁን በወጣው ማሻሻያ መሰረት የካናቢስ እጽ በመጠቀም ለእስር ተዳርገው የነበሩ ከ4 ሺህ በላይ ታይላንዳውያን እንደሚፈቱም የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
ታይላንድ በፈረንጆቹ በ2018 ካናቢስ ለህክምና አገልግሎት እንዲውል የፈቀደች የመጀመሪያዋ ሀገር እንደነበረች አይዘነጋም፡፡
በታይላንድ ካናቢስን እንደ ባህላዊ ህክምና የመጠቀም ባህል የቆየ መሆኑም እንዲሁ የሚታወቅ ነው ፡፡