የኢትዮጵያ መንግስትም በአፍሪካ ህብረት በኩል ከህወሓት ጋር እንዲደራደር የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አስታውቋል
ህወሓት የአፍሪካ ህብረት በደቡብ አፍሪካ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዲደራደር ያቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትም በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ በአፍሪካ ህብረት በኩል ከህወሓት ጋር እንዲደራደር የቀረበለትን ጥሪ መቀበሉን አስታውቋል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ህወሓት የተደራዳሪ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት ለቀረበላቸው የድርድር ጥሪ ምስጋና ያቀረቡት ቃል አቀባዩ ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በታቀደው ድርድር ይሳተፋል ብለዋል፡፡
ግጭት ማቆም የድርድሩ አጀንዳ መሆኑን ማወቅ ቢቻል ጠቃሚ ይሆን ነበር ያሉት ቃል አቀባዩ ግልጽ እንዲሆኑልን እንፈልጋለን ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡፡
በድርደሩ እንደ ታዛቢ፣ ተሳታፊ እና ዋስትና ሰጭ የሚጋበዙ ተጨማሪ አካላት ስለመኖራቸው እንዲሁም የአለምአቀፉ ማህበረሰብ ስለሚኖረው ሚና ማብራሪያ እንደሚገልግ አቶ ጌታቸው ረዳ ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የህወሓት ተደራዳሪ ቡድኑ የጸህንነት ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በድጋሚ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመደራደር ፍቃደኝቱን የገለጸው ህወሓት ጌታቸው ረዳን እና ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያከተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ህብረት ጥሪ መንግስት ከዚህ በፊት ሲያራምድ የነበረውን አቋም የጠበቀ ነው ብሏል፡፡
መንግስት ንግግሩ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆንና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ መንግሥት አቋሙን ሲገልጥ ቆይቷል፡፡
መንግስት በዛሬው መግለጫው ጦርነቱ ድጋሚ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚደረገው ድርድር ዝግጁ መሆኑን ግልጽ አድርጓል።
ጦርነቱ በነሀሴ ወር ከመቀስቀሱ በፊት በአፍሪካ ህብረት የአደራዳሪነት ሚና ላይ ጥያቄ ሲያነሳ የነበረው ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር እንደሚፈልግ ከሳምንት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ህወሓት ጋር የገባው ጦርነት ከተጀመረ ሁሉት አመቱን እያገባደደ ነው፡፡