ከደራ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ከታገቱ ዜጎች ውስጥ 360 መለቀቃቸው ተገለጸ
ከደራ በፍቼ በኩል ወደ አዲስ አበባ በሚያስኬደው መስመር ላይ የፌዴራል የጸጥታ ኃይል እንዲሰማራ ወረዳው ጠይቋል
የደራ፣ ፍቼ አዲስ አበባ መንገድ ለስምንት ወራት ተዘግቶ ነበር
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኘው የደራ ወረዳ አስተዳደር በአዲስ አበባ ፍቼ ደራ መስመር የፌዴራል የጸጥታ ኃይል እንዲሰማራ ጠየቀ።
የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ ውብሸት አበራ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የደራ ፍቼ አዲስ አበባ መስመር ላለፉት ስምንት ወራት ተዘግቶ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዋና አስተዳዳሪው የመኪና መንገዱ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም ትናንት ሰዎች ግን መታገታቸውን ገልጸዋል።
ትናንትና አራት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና አንድ የጭነት መኪና መታገታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው አሁን ላይ የመከላከያ ሰራዊትና የፌዴራል ፖሊስ በኣባቢው እንዲሰማራ ጠይቀዋል።
ዋና አስተዳዳሪው የፌዴራል ሰራዊት እንዲሰማራ በተደጋጋሚ ለሰላም ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረባቸውን እና ምላሽ እንዳላገኙ ልጸዋል።
ከደራ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ከታገቱ ዜጎች መካከል እስካሁን 360 ዎቹ የክልሉ መንግስት የፀጥታ ኃይሎች በሰሩት ስራ መለቀቃቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ አጋቾቹ ደግሞ በራሳቸው አንድ ወንድ እና አንድ ሴት መልቀቃቸውን ገልጸዋል።
አሁንም 10 ሰዎች መታገታቸውን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው አጋቾቹ ብር እንደሚፈልጉም ገልጸዋል። ትናንት በስፍራው ከታገቱት ዜጎች ውስጥ ሁለት የደራ ባለሀብቶች እንዳሉበትም ተገልጿል።
የታጋቾችን ብዛትና ማንነት እንዴት እንዳወቁ የተጠየቁት ዋና አስተዳዳሪው አምልጠውና ተለቀው የመጡ ታጋቾች መረጃ እንደሰጡ አቶ ውብሸት ገልጸዋል።
እገታው የተፈጸመው መንግስት ሸኔ፤ እራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን እንደሆነ የገለጹ አቶ ውብሸት እገታው የተፈጸመው ከፍቼ ከተማ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን ገልጸው ነበር።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ትናንትና ይህንን ጉዳይ እንዳልሰሙና በአካባቢው ”ሽፍታ ይንቀሳቀስ ይሆናል” እንጅ ሌላ ችግር የለም ሲሉ ለአል ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል።