በኦሮሚያ ለድልድይ ግንባታ የቴክኒክ ድጋፍ ለማደረግ የሄዱ የመንገዶች ባለስልጣን ባለሙያዎች ተገደሉ
በጥቃቱ የ7 መሃንዲሶች፣ 1 አሽከርካሪና ቡና በማፍላት የምትተዳደር አንድ ሴትን ጨምሮ የ9 ሰዎች ህይወት አልፏል
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገደሉት ሰዎች በዓለም ገና ዲስትሪክት ስር የነበሩ ሰራተኞቼ ናቸው ብሏል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ባለሙያዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት፤ ታጣቂዎቹ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ ቀበሌ ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ነው የባለሙያዎች ህይወት ያለፈው።
ጥቃቱ ባሳለፍነው ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ገደማ ላይ መፈጸሙን አቶ ድሪርሳ ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን የአሸበሪው “የሸኔ” ቡድን አባላት ነው የፈጸሙት ያሉት አስተዳዳሪው፤ በድልድይ ግንባታ ስራ ላይ ተሰማርተው አመሻሽ ወደ ማደሪያቸው በመመለስ ላይ የነበሩ 11 ሰዎችን አሳፍሮ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃቱ መፈጸሙንም ገልጸዋል።
በጥቃቱም በተሸከርካሪው ላይ ከነበሩ 11 ሰዎች ውስጥ 7 የመንገድ ግንባታ መሃንዲሶች፣ 1 የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ አሽከርካሪ እና በድልድይ ግንባታው በተፈጠረ የስራ እድል ቡና በማፍላት የምትተዳደር አንድ ሴትን ጨምሮ የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።
በተሸከርካሪው ላይ የነበሩ ሁለት ሰዎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ማምለጣቸውንም ነው አቶ ድሪርሳ ያስተወቁት።
ጥቃቱን የፈጸመውን የአሸባሪው “የሸኔ” ቡድን ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ያስታወቁት አቶ ድሪርሳ፤ በትናትናው እለትም በሜታ ሮቢ ወረዳ በአካባቢው በሚሊሻዎች እርምጃ እንደተወሰደበት አስታውቀዋል።
በአሁኑ ሰዓትም የክልሉ እና ሌሎችም የፀጥታ አካላት በቡድኑ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ክትትል እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ ጥቃቱ መፈጸሙን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅትም የክልሉ የጸጥታ አካላት ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎቻ ገር በመሆን በአሸበሪ ቡድኑ ላይ እርጅ ለመወውሰድ እሰሩ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ የተገደሉት ሰዎች የዓለምገና ዲሰትሪክት ስር የነበሩ የተቋሙ ሰራተኞች እንደሆኑ እና በደርጊቱ ማዘኑን ለአል አይን አማርኛ ገልጿል።
ባለሙያዎች “ኡርገዓ” በተባለ ወንዝ ላይ በአካባቢው ባለሀብቶች ድጋፍ እና ህብረተሰቡ ተሳትፎ ላለፉት 2 ዓመታት እየተገነባ የነበረ እና ወደ መጠናቀቅ ለደረስ ድልድይ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ይናገራሉ።
የድልድዩ ግንባታ የረጅም ዘመናት የህብረተሰቡ ጥያቄ የነበረ መሆኑን በማስታወስ፤ ባለሀብቱ እና አካባቢው ነዋሪዎች ባሰባሰቡት 200 ሚሊየን ብር በመገንባት ላይ ያለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ድልድዩ የግንደ በረት፣ የአቡና ግንደበረት፣ ሜታ ሮቢ፣ ሜታ ወልቂጤ እና አደዓ በርጋ የተባሉ 5 ወረደዎችን የሚያገናኝ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ግንደበረት ለመሄድ ይወስድ የነበረን 200 ኪሎ ሜትር መንገድ ወደ 80 ዝቅ ያደርግ ነበረም ብለዋል።