በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን በተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የ5 ሰዎች ህይወት አለፈ
ታጣቂዎቹን ለመያዝ የመንግስት የጸጥታ መዋቅር ክትትል እያደረገ መሆኑን ዞኑ አስታውቋል
ጥቃቱ ትናንት ከምሽቱ 4:30 አካባቢ ነው በኩዩ እና በደገም ወረዳዎች መካከል ለጊዜው ባልታወቁ ታጣቂዎች የተፈጸመው
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ታጣቂዎች በተሽከርካሪዎች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡
ጥቃቱ ትናንት ምሽት ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም ሲጓዙ በነበሩ የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች ላይ ነው የተፈጸመው ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ለኢቢሲ ማብራሪያ እንደሰጡት የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ቅናጢ ጫላ ገለጻ፡፡
ጥቃቱ ምሽት 4፡30 አካባቢ ለጊዜው ባልተያዙ እና ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች የተፈጸመ ነው ያሉት ኃላፊው በደገም እና ኩዩ ወረዳዎች መካከል በ6 የአይሱዙ ተሽከርካሪዎች ላይ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ “የ5 ሰዎች ህይወት አልፏል”ም ነው አቶ ቅናጢ ያሉት።
ሁለት አይሱዙዎች እርስ በእርስ በመጋጨታቸው አንዱ ደግሞ በመገልበጡ ምክንያት በሶስት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ተናግረዋል፡፡
ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ተስተጓጉሎ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ተመልሷል እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፡፡
አቶ ቅናጢ ጥቃት አድራሾቹን ለመያዝ በመንግስት የጸጥታ መዋቅር በኩል ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ለዚህም የቤት ለቤት አሰሳን ጨምሮ የተለያዩ የክትትል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ከአሁን ቀደምም በአካባቢው እንዲሁ ዓይነት ችግሮች ማጋጠማቸው የሚታወስ ነው፡፡