ከደራ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ያሉ የሕዝብና የጭነት ተሸከርካሪዎች ከነ ተሳፋሪዎቻቸው መታገታቸው ተገለጸ
የደራ፣ ፍቼ አዲስ አበባ መንገድ ለስምንት ወራት ተዘግቶ ነበር
እገታው የተፈጸመው ከፍቼ 28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ተብሏል
ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ወደ አዲስ አበባ እየመጡ የነበሩ አራት የሕዝብ ማመላለሻና አንድ የጭነት ተሸከርካሪዎች መታገታቸው ተሰማ።
ተሳፋሪዎቹ ከደራ ወረዳ ጉንዶ መስቀል ከተማ ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ላይ ሳሉ መታገታቸው ነው የተገለጸው።
ተሳፋሪዎቹ የታገቱት ደራ ወረዳን አልፈው ሂደቡአቦቴ ወረዳ ኤጀሬ ከተማ ሊገቡ ሲሉ ጥቂት ሲቀራቸው እንደሆነም የዐይን እማኞች ገልጸዋል።
ተሸከርካሪዎቹ ከነተሳፋሪዎቻቸው የታገቱት በሂደቡአቦቴ ወረዳ ወዘሚ በሚባል መንደር ውስጥ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩት።
እገታው የተፈጸመው ከፍቼ ከተማ በ 28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲሆን ፤ ተሳፋሪዎቹ መንገድ የጀመሩት ደግሞ ከፍቼ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው የደራ ወረዳ ዋና ከተማ ከጉንዶ መስቀል ነው።
አቶ ስለሺ ደግዋለ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ታጋቾቹ ወዲያውኑ ስልክ ሲደወልላቸው ይጠራ እንደነበር፤ይሁንና ከቆይታ በኋላ የታጋቾቹ ስልክ እንደማይሰራ ምናልባትም ስልክ ሳይቀሙ እንዳልቀረ ነው የዐይን እማኙ የገለጹት።
የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ ውብሸት አበራ አራት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና አንድ የጭነት መኪና መታገታቸውን ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል። ዋና አስተዳዳሪው እገታው የተፈጸመው በኦሮሚያ ክልል ሂደቡአቦቴ ወረዳ ኤጀሬ ከተማ አቅራቢያ እንደሆነም ገልጸዋል።
የመንግስት የጸጥታ ኃይል ወደስፍራው መሄዱን ያነሱት አቶ ውብሸት እስካሁን 230 ሰዎች ከእገታው መለቀቃቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በተሸከርካሪዎቹ ውስጥ ምን ይህል ሰዎች እንደተሳፈሩ ከጉንዶ መስቀል መረጃ እየሰበሰቡ እንደሆነ ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው የተለቀቁ ቢኖሩም አሁንም የታገቱ እንዳሉ ማወቃቸውን ተናግረዋል።
እገታው የተፈጸመው መንግስት ሸኔ፤ እራሱን ደግሞ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ቡድን እንደሆነም ነው አቶ ውብሸት የገለጹት። ተሸከርካሪቹ የታገቱበት አካባቢ በብዛት ቡድኑ የሚንቀሳቀስበት ስለመሆኑም ነው የገለጹት።
እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ከእገታው ያልተለቀቁ አሽከርካሪዎችና ሌሎች ሰዎች እንዳሉ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው ብዛታቸውን ግን በትክክል መግለጽ አስቸጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።
ስማቸው እንድጠቀስ ያልፈለጉ አስተያየት ሰጭዎች ደግሞ፤ ከእገታው ያመለጡ ሰዎች እንዳሉ ተናግረው አብዛኞች ታጋቾች ግን በኩዩ፣ በአቦቴና በወረጃርሶ ወረዳዎች መካከል ወደሚገኝና ጨለንቆ ወደ ሚባል ቦታ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪም የታገቱት ሰዎች ጨለንቆ እንደተወሰዱ ገልጸው በስፍራው መንግስት “ሸኔ”፤ እራሱን ደግሞ “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራው ቡድን ማሰልጠኛ እንዳለው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ይህንን ጉዳይ እንዳልሰሙና በአካባቢው ”ሽፍታ ይንቀሳቀስ ይሆናል” እንጅ ሌላ ችግር እንደሌለ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
የደራ ፍቼ አዲስ አበባ መንገድ ለስምንት ወራት ያህል ተዘግቶ የነበረ ሲሆን አገልግሎት መስጠት የጀመረው በቅርቡ እንደሆነ የደራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውብሸት አበራ እና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።