በካርቱም የተጠራው ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ ያሰጋው የሱዳን መንግስት ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ድልድዮችን ዘጋ
በሚሊየን የሚቆጠሩ ሱዳናውያን የሚሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ በካርቱም ተጠርቷል
የካርቱም የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪውን ተከትሎ በሀገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎትም እንዲቋረጥ ተደርጓል
በሱዳኗ ዋና ከተማ ካርቱም በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚደረግ ተነግሯል።
የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪውን የስተላፉትም የሱዳን የተቃዋሚዎች እና የፖለቲካ ሀይሎች ኮሚቴ ሲሆን፤ ሰልፉም በሌተናል ጄነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን እና በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ መካከል የተደረሰውን ስምምነት በመቃወም ነው የሚካሄደው።
የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪውን ተከትሎም በካርቱም ውስጥ የሚገኘው የደህንነት ኮሚቴ፤ ከህላፋያና ሶባ ድልድዮች ውጪ በሶስት አቅጣጫዎች ወደ ከተማይቱ የሚያስገቡ ድልድዮችን ከትናንት ምሽት ጀምሮ እንዲዘጉ ውሳኔ አሳልፏል።
ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ተቋማት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ያሳሰበው ኮሚቴው፤ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ በመብት ቢሆንም፤ አመጽ እና ሁከት መቀስቀስን ግን እንደማይታገስ አስታውቋል።
በካርቱም ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ጥሪውን በመከተል የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንም ከስፍራው የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በሱዳንት የህዝባዊ አመጽ እና ተቃውሞ የተጀመረበትን ዓመት ለማስታወስ በተደረገው ሰለፍ ላይ ሰልፈኞች ድልድዮችን ለመዝጋት የተመደቡ የፀጥታ ሀይሎችን በማለፍ የሀገሪቱን ፐሬዚዳንት ቤት መንግስት ከበው እንደነበረ ይታወሳል።
በአሁኑ ወቅትም ሰልፈኞቹ ወደ ካርቱም ከተማ አልፈው እንዳይገቡ በማሰብ ኮንቴይነሮችን ጭምር በመጠቀም ድልድዮች መዘገታቸውን የሚያመላክቱ ፎቶዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተለቀዋል።
ሱዳናውያን ሰልፈኞች ባሳለፍነው ሳምንት ባካሄዱት የተቃውሞ ሰልፍ በካርቱም የሚገኘውን የሀገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱን ሊቀ መንበር አብዱል ፋታህ አልቡርሃንን ቤተ መንግስት መክበባቸውን ይታወሳል።
ሰልፈኞቹ በሳለፍነው ሳመንት እሁድ ባደረጉት ሰልፍ ላይ ባሰሙት መፈክሮችም የሃገሪቱን ጦር ድርጊቶች አውግዘዋል፣ ወታደራዊ ግዞት በቃንም ብለዋል።
የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በትንሹ 123 ሰዎች ተጎድተዋል መባሉ ይታወሳል።