በተቃውሞ ሰልፉ ላይ 114 ዜጎች በፖሊስ ተይዘው ታስረዋል ተብሏል
በሱዳን በተከሄደው የተቃውሞ ሰልፎች ላይ 58 ፖሊሶች መጎዳታቸው ተገልጿል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ የሱዳን ጦር በሲቪል አስተዳድሩ ላይ መፈንቅለ መንግስት መፈጸሙን እና ስልጣን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሱዳናዊያን ወደ የአደባባይ ተቃውሞ ማሰማታቸው ቀጥለዋል፡፡
ሱዳናዊያን በተደጋጋሚ ባደረጉት የተቃውሞ ሰልፎች የሱዳን ጦር የሲቪል አስተዳድሩን ወደ ስልጣን ቢመልስም በጀነራል አልቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ ጦር ሙሉ ለሙሉ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳድር እንዲያስረክብ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ በሁሉም የሱዳና ዋና ዋና ከተሞች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ወደ አደባባይ የወጣ ሲሆን ሰላማዊ ሰልፉን ለመጠበቅ ከተሰማሩ ፖሊሶች መካከል 58 ያህሉ በሰላማዊ ሰልፈኞች መጎዳታቸውን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፤
ፖሊስ በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ህግ ጥሰዋል ያላቸውን 114 ሰዎች ማሰሩንም ተገልጿል፡፡
የሱዳን ጦር የቅዳሜውን ሰላማዊ ሰልፍ ለመከልከል በርካታ አባላቱን ያሰማራ ሲሆን ወደ ቤተመንግስት የሚያስኬዱ ዋና ዋና መንገዶችን እና ድልድዮችን አስቀድሞ ዘግቶ ነበር፡፡
የሱዳን ጦር በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን ሙሉ ለሙሉ ቢቆጣጠርም ሱዳናዊያን እና ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ ድርጊቱን በመቃወማቸው ይዞት የነበረውን ስልጣን በከፊል ለመመለስ ተገዷል፡፡
ይሁንና ሱዳናዊያን የሱዳን ጦር ሙሉ ለሙሉ ከስልጣን ተነስቶ ድንበር በመጠበቅ ላይ ብቻ እንዲሰማራ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ካሳለፍነው ጥቅምት ወር ጀምሮ በሱዳን በተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ እስካሁን 48 ሰዎች በጸጥታ ሀይሎች እንደተገደሉ የሱዳን የህክምና ማህበር አስታውቋል፡፡