ሱዳን የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ልትጀምር ነው
የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን በሃምሌ 2023 ይካሄዳል ላለው ምርጫ ከቀጣዩ ዓመት ጥር ጀምሮ ዝግጅቶች መደረግ እንደሚጀምሩ አስታውቋል
የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ከወዲሁ ተግባራዊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ እንዲጀምሩ አዟል
ሱዳን ለቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ ልትጀምር ነው፡፡
በሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ከወዲሁ ተግባራዊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ እንዲጀምሩ አዟል፡፡
ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች የመከረው ምክር ቤቱ በምርጫ ሂደቶች ላይ መክሯል፡፡
ምክር ቤቱ ጦሩ በወሰደው እርምጃ ተወግደው ወደነበሩበት ስልጣን የተመለሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ስልጣን እንደሚለቁ ባሳወቁ በቀናት ውስጥ ነው የተሰበሰበው፡፡
የጦሩን ጣልቃ ገብነት የኮነኑት ሃምዶክ የሲቪል መንግስትን ለማቋቋም መቸገራቸውን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ሲወጡ ነበር፡፡
የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን የጊዜ ሰሌዳ በፈረንጆቹ ሃምሌ 2023 ለማካሄድ ለታሰበው ሃገራዊ ምርጫ ከቀጣዩ ዓመት ጥር 2022 ጀምሮ ዝግጅቶች እንደሚደረጉ ያሳያል፡፡
ኮሚሽኑ የምርጫውን የአተገባበር እቅዶችን በተመለከተ ለሉዓላዊ ምክር ቤቱ አብራርቷል፡፡
ለምርጫው አሳታፊነት ከወዲሁ እንዲሰራ ያዘዘው ሉዓላዊ ምክር ቤቱም ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጀመሩ አቅጣጫን አስቀምጧል፡፡ ከወዲሁ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች እንዲሰሩም አዟል፡፡
ምክር ቤቱ በሰሞነኛ የዳርፉር እና ሌሎች ተቃውሞዎቹን ተከትለው ባጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችም ላይ ተወያይቷል፤ እንደ ሃገሪቱ ዜና አገልግሎት ዘገባ፡፡
ከሳምንት በፊት ከተካሄዱ ተቃውሞዎች ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን እንደሚያጣራም ጭምር ነው ምክር ቤቱ የገለጸው፡፡
በሰልፈኞች ላይ የሚወሰዱ ያልተመጣጠኑ የኃይል እርምጃዎችን ያወገዘው ተመድ አስገድዶ መድፈር ተፈጽሟል ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
13 ሴት ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች ተደፍረዋል መባሉም አይዘነጋም፡፡