ቤተ መንግስት በተከበበበት በትናንቱ የሱዳን ተቃውሞ በትንሹ 123 ሰዎች ሳይጎዱ አልቀረም ተባለ
የሃገሪቱን ብሔራዊ ቤተ መንግስት መክበባቸው ተነግሮ እንደነበርም ይታወሳል
በሃገሪቱ ወታደራዊ አገዛዝ እንዲያበቃ የጠየቁ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ትናንት ጎዳናዎችን ማጥለቅለቃቸው ይታወሳል
ትናንት እሁድ ካርቱምን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን ባዳረሰው ተቃውሞ በትንሹ 123 ሱዳናውያን ሳይጎዱ እንዳልቀረ የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሱዳናውያኑ የጸጥታ ኃይሎች ተቃዋሚዎቹን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉም ነው የተነገረው፡፡ መጎዳታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ወታደራዊ አገዛዝን እና በቅርቡ በእነ ሌ/ጄ አል ቡርሃን የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም ወደ አደባባዮች የወጡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ትናንት የሃገሪቱን ብሔራዊ ቤተ መንግስት ጭምር ሳይቀር ከበው ነበረ፡፡
ወደ ካርቱም የሚያስገቡና የሚያስወጡ ዋና ዋና መንገዶችን ይዘጉ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
ከሰልፈኞቹ አንዳንዶቹ ወደ ቤተ መንግስቱ ለመግባት መሞከራቸውን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡
አስለቃሽ ጋዝን ጨምሮ ጥይት ይተኩሱ እንደነበርም አል ሃዳስን ጨምሮ የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
በዚህ መካከል በትንሹ 123 ሰዎች ሳይጎዱ እንዳልቀረም ነው የሃገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀው፡፡
በጦሩም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በሚመራው መንግስት መካከል የሚደረጉ ምንም ዐይነት ስምምነቶችን አንቀበልም ያሉት ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡
ሰልፉ አል በሽር ከስልጣን የወረዱበት ህዝባዊ አመጽ የተጀመረበትን ሶስተኛ ዓመት ታሳቢ ያደረገም ሲሆን በቡርሃን የሚመራዊ የሃገሪቱ ወታደር ስልጣን ከያዘበት ካሳለፍነው ጥቅምት ወዲህ የተካሄደ ትልቁ የተቃውሞ ሰልፍ ነው ተብሏል፡፡
“አቋማችን ግልጽ ነው፤ ከጦሩ ጋር ምንም ዐይነት ሽርክናም ሆነ ስምምነት አይኖረንም፤ ወታደራዊውን አገዛዝ መቃወማችን ይቀጥላል”ም ነው የህዝባዊ እምቢተኝነቱ መሪዎች ያሉት፡፡
አንዳንዶቹ ረጅም ርቀቶችን አቆራርጠው ነው ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ወደ ካርቱም የመጡት፡፡
መፈንቅለ መንግስቱን ያካሄደው ጦሩ ሃምዶክን ወደ ቀደመ ስልጣናቸው መመለሱ የሚታወስ ነው፡፡