በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያሳፈረች ጀልባ ተገልብጣ በጥቂቱ የ39 ሰዎች ህይወት አለፈ
260 ስደተኞችን ያሳፈረችው ጀልባ በየመን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ነው በከባድ ንፋስ ምክንያት የተገለበጠችው
በአደጋው እስካሁን የ78 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ የተቻለ ሲሆን፥ ከ100 በላይ ስደተኞች የደረሱበት አልታወቀም ተብሏል
የምስራቅ አፍሪካ ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በየመን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ ተገልብጣ በጥቂቱ የ39 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አስታወቀ።
ከአደጋው የተረፉ ሰዎች ጀልባዋ 260 ሰዎችን ጭና እንደነበርና አብዛኞቹም ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለዋል።
ጀልባዋ ከየመን ዋና ከተማ ኤደን በስተምስራቅ ሻብዋ በተባለችው ግዛት የባህር ዳርቻ ከመድረሷ በፊት ነው በከባድ ንፋስ ምክንያት የተገለበጠችው።
አደጋው የደረሰበት አካባቢ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሬውተርስ እንዳስነበበው፥ አሳ አስጋሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች የ78 ሰዎችን ህይወት ማትረፍ የቻሉ ሲሆን፥ ከ100 በላይ የሚሆኑ የጀልባዋ ተሳፋሪዎች እስካሁን የገቡበት አልታወቀም ተብሏል።
የነፍስ አድን ሰራተኞችም የጠፉትን ስደተኞች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን የአለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) አስታውቋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የሃውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ቢጠናከርም በርካታ ስደተኞች በየመን በኩል ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በጀልባ መጓዛቸውን አላቋረጡም።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው ባለፈው አመት ብቻ ከምስራቅ አፍሪካ የተነሱ 97 ሺህ ስደተኞች የመን ደርሰዋል።
የአለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትም በየአመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ከኢትዮጵያ የሆኑ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች በየመን በኩል ወደ ሳኡዲና የተለያዩ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለመግባት እንደሚሞክሩ ነው ያስታወቀው።
በየመን ያለው ሁኔታ ጉዟቸውን ሲያሰናክለውም ጊዜ ለመግዛት ወደ ጅቡቲ ይመለሳሉ።
ለህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው ፈታኙን ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች በጀልባ መስመጥና መገልበጥ ህይወታቸውን እየተነጠቁ መሆኑን የምትገልጸው ኢትዮጵያ፥ ዜጎች ከህገወጥ ጉዞ እንዲቆጠቡ ስታሳስብ መቆየቷ ይታወሳል።
ከወራት በፊት በጅቡቲ የባህር ዳርቻ አካባቢ በደረሱ አደጋዎች 60 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ማለፉ አይዘነጋም።