አሜሪካ ሶስት የሃውቲ ታጣቂዎችን ጀልባዎች መትቼ አሰመጥኩ አለች
በሄሊኮፕተር የተመቱት ጀልባዎች በሲንጋፖር የተመዘገበች መርከብን ለማገት መሞከራቸው ተገልጿል
የየመን ሃውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ያሏቸውን መርከቦች በመምታት ላይ ናቸው
አሜሪካ በቀይ ባህር ሶስት የሃውቲ ታጣቂዎችን ጀልባዎች መምታቷን አስታወቀች።
የሃውቲ ታጣቂዎች ከተቆጣጠሩት አካባቢ የተነሱ አራት ጀልባዎች በሲንጋፖር የተመዘገበች የንግድ መርከብን ለማገት ሙከራ ማድረጋቸውንም ነው የአሜሪካ ጦር የገለጸው።
እየተኮሱ የተጠጉት ጀልባዎች ከመርከቧ በሜትሮች ልዩነት ነበሩ ያለው ጦሩ፥ መርከቧ ባሰማችው የድረሱልኝ ጥሪ የአሜሪካ ባህር ሃይል ሄሊኮፕተሮች ደርሰው ሶስቱን ከጥቅም ውጭ እንዳደረገቻቸው ገልጿል።
ጀልባዎቹ ሰጥመው ያሳፈሯቸው ሁሉም ሰዎች መሞታቸውንና አራተኛዋ ጀልባ ግን ከአካባቢው በፍጥነት መሰወሯንም የአሜሪካ ማዕከላዊ እዥ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
በሲንጋፖር ተመዝግባ በዴንማርክ ኩባንያ የምትተዳደረው “ማይርስክ ሃንግዙ” መርከብ ያስተናገደችውን ጥቃት ተከትሎ ግዙፉ የመርከብ ኩባንያ ማይርስክ በቀይ ባህር የሚያደርገውን ጉዞ ለ48 ስአት አቋርጧል።
የኩባንያው መርከብ በ24 ስአት ውስጥ ሁለተኛው ጥቃት ነው ዛሬ የደረሰባት።
በኢራን የሚደገፉት የሃውቲ ታጣቂዎች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው ባሏቸው መርከቦች ላይ ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ የቀይ ባህር ውጥረት ነግሶበታል።
አሜሪካ መራሹ የባህር ቅኝት ግብረሃይል ከተሰማራ በኋላ ግን መረጋጋት እየታየ ነው ተብሏል።
የሃውቲ ታጣቂዎች ከህዳር 19 2023 ጀምሮ 23 የመርከብ ጥቃት ሙከራዎችን ማድረጋቸውን የገለጸው የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ፥ ጥቃቱ የጋራ የቅኝት ግብረሃይሉ ወደ ስራ ከገባ በኋላም ቀጥሏል ብሏል።
ግብረሃይሉ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ 1 ሺህ 200 የንግድ መርከቦች በቀይ ባህር ጉዞ ማድረጋቸውን በመጥቀስ የሃውቲዎች የድሮን ወይም የሚሳኤል ጥቃት ያደረሰው ጉዳት እንደሌለም አብራርቷል።
የየመኑ ቡድን ግን እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ እየፈጸመችው ያለውን ድብድባ ካላቆመች ጥቃቴን እቀጥላለሁ የሚል ዛቻውን አሰምቷል።