በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከ30 ሚሊዬን የሚልቁ አፍሪካውያን ስራ አጥ ሆነዋል ተብሏል
በተያዘው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት (2021) 39 ሚሊዬን አፍሪካውያን ለከፋ ድህነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ የአፍሪካ ልማት ባንክ አስታወቀ፡፡
የባንኩ ፕሬዝዳንት ናይጄሪያዊው አኪንዊሚ አዴሲና ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የደቀቀው የአህጉሪቱ ምጣኔ ሃብት 39 ሚሊዬን ገደማ ዜጎችን ወደ ከፋ የድህነት አዘቅት ሊገፋ ይችላል ብለዋል፡፡
አኪንዊሚ በበይነ መረብ በተካሄደው የአፍሪካ ሲንጋፖር የቢዝነስ ፎረም ላይ ተሳትፈዋል፡፡
በውይይቱ የወረርሽኙ እጅግ አስከፊ ጎን ዜጎችን ተጽዕኖ ላይ መጣሉ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከ30 ሚሊዬን የሚልቁ ሰዎች ስራ አጥ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በአህጉሪቱ ሊኖር የሚችለው የውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ሊያድግ እና የየሃገራቱ ምጣኔ ሃብት ሊነቃቃ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
አፍሪካ “ጠንካራ እና ጥራት ያለው” መሠረተ ልማትን ለመገንባት ብትችል የተቀረውን አለም ቀልብ ልትስብ እንደምትችልም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡ ለዚህም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአፍሪካ 7 ነጥብ 6 ሚሊዬን ዜጎች ለወረርሽኙ መጋለጣቸውን የአህጉሪቱ በሽታዎች ቁጥጥር ማዕከል መረጃ ያመለክታል፡፡