ምስራቅ አፍሪካ ኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በ4 ነጥብ 2 ሚሊየን ጎብኚዎች ይጎበኙ ነበር
የኮሮና ቫይረስ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ቱሪዝም ላይ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማሳጣቱ ተገለጸ።
የምስራቅ አፍሪካ ቢዝነስ ምክር ቤት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የኮሮና ቫይረስ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ባደረሰው ጉዳት 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አሳጥቷል።
ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጎብኚዎች ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገራት ይመጡ እንደነበር ተገልጿል።
ከገቢው በተጨማሪም በቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርተው የነበሩ 2 ሚሊዮን ዜጎች ኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ጉዳት እና ጎብኚዎች በቤታቸው በመቀመጣቸው ምክንያት ስቸውን እንዳጡ ሪፖርቱ ገልጿል።
ቱሪዝም ዘርፍ ለምስራቅ አፍሪካ አገራት አመታዊ ኢኮኖሚ የ10 በመቶ ድርሻ የነበረው ሲሆን የቫይረሱ ጉዳት መቀጠሉ ጉዳቱ አሁንም ይጨምራል ተብሏል።
ይህ ዘርፍ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በፊት ለ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዝቅ ማለቱንም ሪፖርቱ ያስረዳል ሲል ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
ብሔራዊ ፓርኮችን የሚጎበኙ ቁጥር በ65 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ይህ መሆኑ ደግሞ የዱር እንስሳት ጥበቃ ስራዎችን አደጋ ላይ እየጣለ ነውም ተብሏል።
የአውሮፓ፤አሜሪካ፤እስያ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጎብኚዎች በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን የሚጎበኙ ዜጎች ናቸው።