በጋዛ ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የተደረሰው ስምምነት ተግባራዊመ መደረግ ጀመረ
እስራኤልና ሃማስ ለ4 ቀናት የደረሱት ስምምነት ዛሬ ጠዋት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል
ተኩስ አቁሙ ተግበራዊ በሚሆንበት ጊዜ ሃማስ 50 ተጋቾችን ይለቃል ተብሏል
እስራኤልና ሃማስ በጋዛ ለአራት ቀናት የተኩስ አቁም ለማድረግ የደረሱት ስምምነት ዛሬ ጠዋት ላይ ተግባራዊ መደረግ ጀመረ።
ለአራት ቀናት የሚቆየው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዛሬ አርብ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን፤ በእዚህ ቀናትም ሃማስ ያገታቸውን በርካታ ታጋቾች እንደሚለቅና እስራኤልም በምትኩ ያሰረቻቸውን ፍሊስጤማውያን እንደምትለቅ ይጠበቃል።
በስምምነቱ መሰረትም ሃማስ 50 ታጋቾችን ይለቃል የተባለ ሲሆን፤ እስራኤል ደግሞ 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመፍታት ተስማምታለች ተብሏል።
በስምምነቱ መሰረት ሃማስ በየቀኑ 10 ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን፥ እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆምና ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትፈታ ይጠብቃል።
የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ አል ቃሳም ብርጌድ ስምምነት መደረሱን ያረጋገጠ ሲሆን፤ በዛሬው እለትም 13 ታጋቾችን እንደሚለቅ ነው ያስታወቀው።
በተጨማሪም የተኩስ አቁም ስምምነቱ በጋዛ ውስጥ ለሚኖሩ 2.3 ሚሊየን ሰዎች ከእስራኤል የአየር ድብደባ እፎይታን የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰብአዊ ድጋፍን የጫኑ ተሽከርካሪዎችም ወደ ጋዛ ይገባሉ ተብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በረቡዕ መግለጫቸው በሃማስ ላይ “ፍጹም ድል” እስክንጎናጸፍ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸው ይታወሳል።
በትናንትናው እለትም በካሃን ዮኒስ እና በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የ14 ሺህ ፍልስጤማውያን እና 1 ሺህ 200 እስራኤላውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ዛሬ 48ኛ ቀኑን ይዟል።