እስራኤል በትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው የቦምብ ጥቃት ከ200 በላይ ንጹሃን ተገደሉ
ግብጽ የቴል አቪቭን እርምጃ ያወገዘች ሲሆን በንጹሃን ላይ የተፈጸመው “የጦር ወንጀል” ሊመረመር ይገባል ብላለች
ኳታርም የመንግስታቱ ድርጅት ገለልተኛ ቡድን ወደ ስፍራው በማቅናት ጥቃቱን እንዲመረምር ጠይቃለች
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በሚገኘው አል ፋኩራ ትምህርት ቤት በፈጸመችው ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 ማለፉ ተነግሯል።
ቴል አቪቭ ስለጥቃቱ ምርመራ ይደረጋል ከማለት ውጭ ማብራሪያ ባትሰጥም የተለያዩ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት እየከሰሷት ነው።
ግብጽ የትናንቱን የአል ፋኩራ ትምህርት ቤት የቦምብ ጥቃት ካወገዙት ሀገራት መካከል ትገኝበታለች።
ተፈናቃዮችን ያስጠለለው ትምህርት ቤት ኢላማ ተደርጎ ንጹሃን መገደላቸው “ሌላኛው የጦር ወንጀል ነው” ያለችው ካይሮ፥ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂ የሚሆን አካል ሊኖር እንደሚገባ አሳስባለች።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፥ በተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ የሚተዳደርን ትምህርት ቤት (ወደ መጠለያነት የተቀየር) በቦምብ መደብደብ ለመንግስታቱ ድርጅትና በስሩ ለሚገኙ ተቋማት ስድብ ነው ብሏል።
የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ ሰርጥ የንጹሃንን ሰቆቃ ለማስቆም በፍጥነት ጣልቃ እንዲገባ ማሳሰቡንም ሽንዋ ዘግቧል።
ኳታርም የመንግስታቱ ድርጅት ገለልተኛ ቡድን ወደ ስፍራው በማቅናት ጥቃቱን እንዲመረምር ጠይቃለች።
የእስራኤል “ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች መቀጠላቸው አሳሳቢ ነው” ያለችው ዶሃ፥ እስራኤል በ24 ስአት ውስጥ ሁለተኛውን ትምህርት ቤት (አል ፋኩራ) መደብደቧን አስታውቃለች።
4 ሺህ ተፈናቃዮችን ያስጠለለው ዛይቶን የተሰኘ ትምህርት ቤት ከትናንት በስቲያ በቦምብ ተደብድቦ በርካቶች ህይወታቸው ማለፉን የመንግስታቱ ድርጅት መግለጹ ይታወሳል።
44ኛ ቀኑን የያዘው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት የንጹሃን ህይወትን መቅጠፉና ጋዛን ማፈራረሱን ቀጥሏል።