እስራኤል እና ሀማስ በጊዜያዊነት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ
የፍልስጤሙ ቡድን ሀማስ በእስራኤል እስርቤት ያሉ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል
በስምምነቱ መሰረት ሀማስ በእጁ ካሉት ታጋቾች ውስጥ 50ዎቹን የሚለቅ ሲሆን እስራኤል ደግሞ በእስር ላይ የነበሩ 150 ፍልስጤማውያን ትለቃለች
እስራኤል እና ሀማስ በጊዜያዊነት ተኩስ ለማቆም ተስማሙ።
እስራኤል እና ሀማስ በዛሬው እለት ለአራት ቀናት ያህል ተኩሱን ጋብ በማድረግ ታጋቾችን በእስረኞች ለመቀያየር መስማማታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በስምምነቱ መሰረት ሀማስ በእጁ ካሉት ታጋቾች ውስጥ 50ዎቹን የሚለቅ ሲሆን እስራኤል ደግሞ በእስር ላይ የነበሩ 150 ፍልስጤማውያን ትለቃለች።
ይህን ሚስጥራዊ ድርድር ሲያካሂዱ የነበሩት የኳታር ባለስልጣናት እንዲሁም እስራኤል፣ ሀማስ እና አሜረካ የስምምነቱ መደረስ አይቀሬ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ጥቃት በከፈተበት ወቅት 200 ገደማ ሰዎችን አግቶ ወስዷል ተብሎ ይታመናል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቢሮ ባወጣው መግለጫ ጦርነቱ ጋብ በሚልበት አራት ቀናት ውስጥ 50 ህጻናት እና ሴቶች ይለቀቃሉ ብሏል።
ስለሚለቀቁት የፍልስጤም እስረኞች ምንም ያላለው መግለጫው ተኩስ አቁም በሚደረግበት በእያንዳንዱ ቀን 10 ታጋቾች እንደሚለቀቁ ገልጿል።
ለሰአታት ዝግ ሆኖ ከቆየው ስብሰባ በኋላ የወጣው ይህ መግለጫ "የእስራኤል መንግስት ሁሉንም ታጋቾች ለማስለቀቅ ቁርጠኛ ነው" ብሏል
የፍልስጤሙ ቡድን ሀማስ በእስራኤል እስርቤት ያሉ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል።
ቡድኑ ወደ ጋዛ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች፣ መድሃኒት እና ነዳጅ እንዲገባም መስማማታቸውን ገልጿል።
ሀማስ እንደገለጸው በአራቱ ቀናት የተኩስ አቁም ጊዜ ውስጥ እስራኤል ምንም አይነት ጥቃት ላትፈጽም ተስማምማለች።
የኳታር መንግስት 50 ሴቶች እና ህጻናት ከጋዛ እንደሚለቀቁ እና በእስራኤል እስር ቤት ያሉ በርካታ እስረኞች በለወጥ አመት እንደሚለቀቁ መተየቢያ ተግረዋል።
ስምምነቱ በተደረሰ በ24 ሰአት ወስጥ ተግባራዊቱ የሚጀመርበት ጊዜ ይፋ ይሆናል ተብሏል።
ይህ ስምምነት ከ13ሺ በላይ ለሆኑ ፍልስጤማውያን ሞት ምክንያት የሆነው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የእስራኤል ትልቁ አላማ አለመቀየሩን ተናግረዋል። ኔታንያሁ ሀማስ እስከሚጠፋ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ብለዋል።