በጋዛ የታገቱ ሰዎች ከአርብ በፊት አይለቀቁም - እስራኤል
እስራኤልና ሃማስ ለአራት ቀናት ተኩስ ለማቆም የደረሱት ስምምነት ከመቼ ጀምሮ እንደሚተገበር እስካሁን በይፋ አልተገለጸም
በጊዜያዊ ስምምነቱ እስራኤል 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች
በሃማስ የታገቱ 50 ሰዎች ከነገ አርብ በፊት እንደማይለቀቁ የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
እስራኤልና ሃማስ ለአራት ቀናት የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ ታጋቾቹ በዛሬው እለት ይለቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።
በኳታር ሸምጋይነት የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት ከዛሬ ጀምሮ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ስምምነት የተደረሰበት ነበር ቢባልም ጦርነቱ እንዳልቆመ ሬውተርስ ዘግቧል።
ሃማስ 50 ታጋቾችን ለመልቀቅ፤ እስራኤል ደግሞ 150 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለመፍታት የተስማሙበት የተኩስ አቁም ስምምነት ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ በይፋ አልተገለጸም።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ዛቺ ሃነግቢ፥ ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የሚደረገው ድርድር መቀጠሉንና ከአርብ በፊት እንደማይለቀቁ ተናግረዋል።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ አንድሬን ዋትሰንም ታጋቾቹን ከጋዛ ለማስወጣት የሎጂስቲክ አቅርቦት እየተመቻቸ እንደሚገኝና ከነገ ጠዋት ጀምሮ እንደሚለቀቁ ገልጸዋል።
ካን የተሰኘው የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን እንደዘገበው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ለአንድ ቀን የተራዘመው ሃማስ እና የኳታር አደራዳሪዎች ፊርማቸውን ባለማስፈራቸው ነው።
በስምምነቱ መሰረት ሃማስ በየቀኑ 10 ታጋቾችን የሚለቅ ሲሆን፥ እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆምና ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትፈታ ይጠብቃል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰብአዊ ድጋፍን የጫኑ ተሽከርካሪዎችም ወደ ጋዛ ይገባሉ ተብሏል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በረቡዕ መግለጫቸው በሃማስ ላይ “ፍጹም ድል” እስክንጎናጸፍ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ማለታቸው ይታወሳል።
በትናንትናው እለትም በካሃን ዮኒስ እና በጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ የአየር ድብደባ መፈጸሟን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የ14 ሺህ ፍልስጤማውያን እና 1 ሺህ 200 እስራኤላውያንን ህይወት የቀጠፈው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ዛሬ 47ኛ ቀኑን ይዟል።