ብሪክስ ለእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈልጋል - ፑቲን
የሩሲያው ፕሬዝዳንት የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ የከሸፈ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማሳያ ነው ብለዋል
የብሪክስ አባል ሀገራት በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ የበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት እንዲረግብ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንቱ የብሪክስ አባል ሀገራት ጉባኤ በበይነ መረብ ሲካሄድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለጋዛ ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሄን ለማፈላለግ የብሪክስ አባል ሀገራት ቁልፍ ድርሻ አላቸው ብለዋል።
“የጋዛ ውጥረት እንዲረግብና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አለማቀፉ ማህበረሰብ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ አለበት፤ ለእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል፤ ለዚህም የብሪክስ አባል ሀገራት ቁልፍ ሚና አላቸው” ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በጋዛ ጉዳይ ላይ ባተኮረው የብሪክስ አባል ሀገራት የበይነ መረብ ውይይት ለመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ አሜሪካን ተጠያቂ አድርገዋል።
የአሜሪካ የከሸፈ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀጠናውን ለትርምስ ዳርጓል ሲሉ የተደመጡት ፑቲን፥ እስራኤል በጋዛ ጦርነቱን እንድታቆም ጠይቀዋል።
ባለፈው ወርም እስራኤል በጋዛ የምድር ውጊያ ስትጀምር የጀርመኑ ናዚ በሁለተኛው የአለም ጦርነት በሌኒንግራድ ንጹሃንን ከጨረሰበት ጥቃት ጋር አገናኝተው ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም።
በትናንቱ ንግግራቸውም በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ህጻናት መገደላቸው “አሰቃቂ” ነው ያሉ ሲሆን፥ ይህ ያለምንም ርህራሄ የሚፈጸም ግድያ “ልዩ ስሜት” ይቀሰቅሳል ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የመንግስታቱ ድርጅት እስራኤልና ፍልስጤም ራሳቸውን የቻሉ ሉአላዊ ሀገር ሆነው ተከባብረው እንዲኖሩ ያሳለፈው ውሳኔ በአሜሪካ ሴራ ተቀልብሶ ከአንድ ትውልድ በላይ ፍልስጤማውያን በጦርነት ውስጥ እንዲኖሩ ተደርጓል ሲሉም አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ብሪክስ ለጋዛው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሄን ለማበጀት ምን አይነት ጥረት እንደሚያደርግ በመልዕክታቸው አላነሱም።
በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የተመሰረተው ብሪክስ በነሃሴ ወር ስድስት ተጨማሪ ሀገራትን አባል ለማድረግ መወሰኑ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ አረብ ኤምሬትስ፣ ኢራን እና አርጀንቲና ስብስቡን የሚቀላቀሉ ሀገራት ናቸው።