በኢትዮጵያ 4 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥረው ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን (Wuhan) ከተማ ነው የተከሰተው፡፡
አሁን ላይ ቫይረሱ ከቻይናና ሁለት የራስ ገዝ አስተዳደር ግዛቶቿ ማካኦ እና ሆንግኮንግን በተጨማሪ 25 ሀገራትን አዳርሷል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን የሟጮች ቁጥር 362 ሲደርስ ተጠቂዎች ከ17380 በላይ ሆነዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ በአሁኑ ወቅትም አራት ሰዎች በበሽታው ተጠርጥረው ፤ አንድ ቻይናዊ እንዲሁም ሶስት ኢትዮጵያውያን፤ አንድ በአክሱም እና ሶስቱ በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
የኖቬል ኮሮና ማረጋገጫ ምርመራ ሪኤጀንት በዓለም የጤና ድርጅት ትብብር አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ በቅርቡ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መሳሪያው በቫይረሱ የተጠቁ ታካሚዎችን በመለየት እና አስፈላጊውን እርዳታ በመስጠት ለወረርሽኝ ቁጥጥር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስትር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እየተወሰዱ ካሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ውስጥ ብሔራዊ ታስክ ፎርስ እና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ስራ ጀምረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አየር መንገድ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መሰጠቱንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ዛሬ 200 የሚሆኑ የሆስፒታል አመራሮች እና ባለሞያዎች በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡
በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እና 27 የተለያዩ የድምበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ እንደሚገኝም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የማጣራት ምርመራው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸውን ተጓዦች የሚለይ ሲሆን ይሄም የቫይረሱ የበሽታ ምልክት የሚያሳዩትን ለመለየት ይረዳል፡፡
እስከ ጥር 24 ቀን2012 ዓ.ም ድረስ 47,162 ተጓዦች የሙቀት መለያ ምርመራ የተደረገላቸው ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 1,695ቱ የመጡት ቫይረሱ ሪፖርት ከተደረገባቸው ሀገራት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ከቻይና የሚመጡ ሁሉንም ተጓዦች በሀገር ውስጥ በሚቆዩበትን ጊዜ፣ አድራሻቸውን እንዲሁም የተለያዩ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝ እስከ 14 ቀን ድረስ የሚከታተል ቡድን ተቋቁሞ እየተከታተለ ይገኛል፡፡ይህም ምልክት በሚያሳዩበት ግዜ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እና ንክኪ ያላቸውን ለመለየት ይረዳል፡፡
ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን (rapid response team) ተዋቅሮ የቫይረሱ ምልክቶችን ጥቆማ በተሰጠ ከ2 ሰዓት ባነሰ ግዜ ውስጥ ማጣራት እንዲችል ለ24 ሰዓት በፈረቃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ ለዚህም ስራ የአየር ማረፊያዎች ፤ ሆስፒታሎች፤ የታክሲማህበራት፤ ኢንደስትሪያል ፓርኮች እና የኮንስትራክሽን ቦታዎች የጠበቀ እይታ አግኝተዋል፡፡
ቫይረሱ አለባቸው ተብሎ የሚጠረጠሩትን ታካሚዎች ህክምና ወደ ሚያገኙበት ቦታ የሚወስዱ 4 ተሸከርካሪዎች(2 ኣምቡላንሶች)ተመድበው ወደ ስራ ተሰማርተዋል፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ በቦሌ ጨፌ ያለው የህክምና ቦታ እና የየካ ኮተቤ ሆስፒታል ለህክምና መስጫነት ተመርጠዋል፡፡
ለጥቆማ እና መረጃ ለማግኘት ነጻ የስልክ መስመር 8335 ከጥር 24/ 2012 ጀምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
እስካሁን 17 ጥቆማዎች የተደረጉ ሲሆን፣ ከነዚህም ስምንቱ በለይቶ ማቆያ ክትትል ሲደረግላቸው ነበር፡፡
ከቻይና ውሃን ግዛት የመጡ እና የመተንፈሻ አካል ህመምና ከፍተኛ ሙቀት ማሳየት የጀመሩ ሁለት ሰዎች እና ከእነርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ተጨማሪ ሁለት ሰዎች ተገኝተው በለይቶ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ክትትል እየተደረገላቸው እንደነበርና ናሙናቸውም ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ጥር 21/2012 ዓ.ም. በምርመራ ውጤቱ ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ስለሆነ በዚያው ቀን ከለይቶ ማቆያ እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ለቤተሰቦቻቸው ሲደረግ የነበረው ክትትል ተቋርጧል፡፡