በኢትዮጵያ 36 የሲቪል ማህበረሰብ ሰራተኞች መገደላቸው ተገለጸ
መንግስት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሰራተኞች ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠይቋል
የሲቪል ማህበረሰብ አዋጁ ቢሻሻል ምህዳሩ ላይ ቀሪ ስራዎች መሰራት አለባቸው ተብሏል
በኢትዮጵያ 36 የሲቪል ማህበረሰብ ሰራተኞች መገደላቸው ተገለጸ
በኢትዮጵያ "አሳሪ" እየተባለ የሚጠራውና በ2001 ዓ.ም. የወጣው የሲቪል ማህበረሰብ ህግ ከተሻሻለ በኋላ አያሌ ድርጅቶች ወደ ስራ ቢገቡም የሀገሪቱ ሰላም እንቅፋት እየሆነባቸው ነው ተብላል፡፡
ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ 36 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሰራተኞች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ለአል ዐይን ተናግራል፡፡
የም/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ መለሰ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ መስራት አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል፡፡
ከአራት ሽህ በላይ ድርጅቶችን በአባልነት የያዘው ም/ቤቱ፤ አባሎቹ እስከ ሞት ድረስ መስዋዕትነት እየከፈሉ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ የተገደሉ የካቶሊክ ሪሊፍ ሰራተኞችን ለአብነት ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት 36 የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ሰራተኞች መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁኔታውን "በጣም አሳሳቢ" ሲሉ የገለጹት ሄኖክ መለሰ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ሰራተኞች "የተለየ ጥበቃ" ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡
"ከቤታቸው ርቀው፤ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰሩ ሰራተኞች የበለጠ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ጥበቃም እንዲደረግላቸው ያስፈልጋል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ማዋከብ ይታያል፡፡ ነገሮች እንዲቆመ ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል፡፡
ከአራት ዓመታት በፊት የተደረገውን የህግ ማሻሻያ በበጎነት የሚያነሱት የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ኃላፊ፤ ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር ላይ ክፍተት አለ ብለዋል፡፡
"አሰሪ፤ ምቹ የስራ ከባቢ ያስፈጋል፡፡ ከግንዛቤ ማነስም ሊሆን ይችላል በተለያየ መልኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰሯቸው ስራዎች እንቅፋቶች አሉባቸው፡፡ ለመቅረፍ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡ ግን ሂደት ነው፡፡ በተለይ ሀገር በችግር በምትወድቅ ጊዜ የሰላም እጦት፤ የእንቅስቃሴ መስተጓጉል ሲኖር ስራቸው በእጅጉ ይገደባል" በማለት ይገልጻሉ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከቀዳማዊ አጼ ኃ/ሰላሴ ዘመን ጀምሮ ሚናቸውን ማሳደጋቸውን ይነገራሉ፡፡ በተለይም ድርጅቶቹ ለሰላም፣ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲና ለልማት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ እያለ ስለመምጣቱ ጠቅሰው፤ ሆኖም የገንዘብ አቅም፣ የፖለቲካ አውድና ሌሎችም ሁነቶች እንቅፋት ሆነዋል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበሰረብ ድርጅቶች ስራ፣ ሚናና ገጽታ በመንግስት የስራ ኃላፊዎችም ሳይቀር የተንሻፈፈ እይታ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡
ሄኖክ መለሰ የሀብት ማመንጨት ላይ በተለይም በማህበረሰቡ የተዛባ አመለካከት እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ድርጅቶቹ ለሁለንተናዊ ለውጥና እድገት ያላቸውን አበርክቶ እንዲወጡ መጠናከር ስለሚገባቸው የሀገር ውስጥ ሀብት አሰባሰብ ላይ መሰራት አንዳለበትም አንስተዋል፡፡
በቀጣዩ ግንቦት ወር የአመለካከት ክፍተቶችን መቅረፍ፣ የትብብርና የአጋርነት ስራዎችን ማሳደግና ምህዳሩን ማስፋት ዓላማ የሰነቀ ዓመታዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡
ሦስተኛው ነው የተባለው መርሀ-ግብሩ፤ ከ200 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይሳተፉበታል ተብሏል፡፡