የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ጻፈ
ምክር ቤቱ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደብዳቤ የጻፈው ኤችአር 6600 እና ኤስ 1339 ረቂቅ ህጎች እንዳያጸድቁት በሚል ነው
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ላሉ ችግሮች በአሜሪካ የተዘጋጁት ሁለቱ ረቂቅ ህጎች መፍትሄ ይሆናሉ የሚል ዕምነት እንደሌለው ምክር ቤቱ ገልጿል
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ለአሜሪካ ፕሬዝዳንት ደብዳቤ ጽፏል፡፡
ምክር ቤቱ ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጻፈው ደብዳቤ ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ሰላና መረጋጋት ለማስፈን በሚል በአሜሪካ ህግ አውጪ አካላት የተዘጋጀውን ረቂቅ ህግ እንዳያጸድቁት ጠይቀዋል፡፡
ምክር ቤቱ አክሎም ፕሬዝዳንት ባይደን ኤችአር 6600 እና ኤስ 1339 በሚል የተዘጋጁትን ረቂቅ ህጎች በጥንቃቄ እንዲያዩትም አሳስቧል፡፡
አሜሪካ በዓለም ላይ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ልማት እና ፍትህ እንዲሰፍን የምትፈልግ ሀገር መሆኗን እንረዳለን ያለው ምክር ቤቱ ኤችአር 6600 እና ኤስ 1339 በሚል የተዘጋጁትን ረቂቅ ህጎች የሚጸድቁ ከሆነ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ እና የተጀመረው የሰብዓዊ ድጋፎችን ለተጎጂዎች የማድረስ ስራዎችን ይጎዳል ሲልም ምክር ቤቱ አክሏል፡፡
እንዲሁም እነዚህ ሁለት ረቂቅ ህጎች ከጸደቁ በኢትዮጵያ ለማካሄድ የታሰበውን ሁሉን አሳታፊ ውይይት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ስራ የሚገድብ እንደሚሆንም ምክር ቤቱ ለፕሬዝዳንት ባይደን በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በኮሮና ቫይረስ እና በድርቅ የተጎዱ በእርዳታ ላይ የተመሰረቱ ሚሊዮን ዜጎች ያሏት አገር መሆኗን የሚጠቅሰው ይህ ደብዳቤ በአሜሪካ የተዘጋጁት ሁለቱ ረቂቅ ህጎች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን ይልቅ የተባባሰ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋልም ብሏል፡፡
ምክር ቤቱ አክሎም ኢትዮጵያ በታሪካዊ መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለች ሀገር መሆኗን ጠቅሶ ትክክለኛ ዲሞክራሲ እና ልማት እንዲመጣ አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ድጋፍ ያስፈልጋል ሲልም በደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እነዚህ ሁለት ረቂቅ ህጎች በኢትዮጵያ ያሉ አሁናዊ ችግሮችን ይፈታሉ ብሎ እንደማያምን የሚጠቅሰው የምክር ቤቱ ደብዳቤ ህጎቹ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳያበላሹም ስጋቱን ጠቅሷል፡፡
የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና እና ዲሞክራሲን ያሰፍናል በሚል የተዘጋጀው ኤችአር 6600 የተሰኘው ረቂቅ ህጉ ላይ ለመምከር የያዘውን ፕሮግራም ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘሙ ይታወሳል፡፡
ኤች አር 6600 በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ተሳታፊ የሆኑ አካላት በዘር ማጥፋት፣በሰብአዊ መብት ላይ በደረስ ጥቃት፤ እና በሌሎች አካባቢዎች በተፈጸሙ ግጭቶች በደረሱ ግፎች ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ግጭቱ እንዲቆም የሚያችል መሆኑን ረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል፡፡