የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫውን ይታዘባሉ ተባለ
“ሱዳን እና ግብጽን በሙሌቱ ላይ ተስማምተን እንፈራረም ብለናቸዋል፤ ነገር ግን የትኛውም ጫና ዋጋ የለውም”- ሚኒስቴሩ
ታዛቢዎችን አልልክም ያለው የአውሮፓ ህብረት የባለሙያዎች ቡድንን እንደሚልክም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል
የአሜሪካ እና የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብን ጨምሮ ዘጠኝ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርጫ የሚታዘቡ የባለሙያዎች ቡድን ‘እንልካለን’ ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር በምታካሂደው ምርጫ፣ በህዳሴ ግድብ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጭ ሚዲያዎች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢትዮጵያ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የምታካሂደው ምርጫ “በሀገሪቱ የምርጫ ታሪክ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል” ብለዋል።
ምርጫውን ለመታዘብ የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ፍላጎታቸውን እየገለጹ መሆኑንም ነው አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በመግለጫቸው ያነሱት።
የአሜሪካ ኤምባሲ እና የብሪታንያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች፣ የሩሲያ ሲቪል ማህበረሰብ፣ የአፍሪካ ህብረት፣ የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ብርጌድ ቲም፣ መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉት 'ናሽናል ዴሞክራሲ' እና 'ኢሎክቶራል ኢንስቲትዩት ፎር ሰስቴኔብል ዴሞክራሲ ኢን አፍሪካ' የተባሉ ተቋማት ምርጫውን ይታዘባሉም ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ታዛቢዎችን እንደማይልክ ቢያስታውቅም የባለሙያዎች ቡድን እንደሚልክ ትናንት መግለጹንም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በሁለት ዓመታት ውስጥ መሙላት ትችል እንደነበረ ነገር ግን ለሁሉም እንደሚበጅ በማሰብ በረጅም ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራች መሆኑንም አስታውቀዋል።
“ሱዳን እና ግብጽን በሙሌቱ ላይ ተስማምተን እንፈራረም ብለናቸዋል” ያሉት አምባሳደር ዲና የትኛውም ጫና ዋጋ እንደሌለውም ተናግረዋል።
“የናይል ወንዝ የአፍሪካ ወንዝ ነው፤ ኢትዮጵያም፣ ግብጽም፣ ሱዳንም አፍሪካዊ ናቸው” ያሉም ሲሆን ኢትዮጵያ የግድቡ ጉዳይ የአፍሪካ ነው ለዚህም በአፍሪካዊ ማዕቀፍ ሊፈታ ይገባል የሚል አቋም እንዳላትም አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ህብረትና አሜሪካ “አሁንም ታዛቢ” መሆናቸውን በማስታወስም ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ማድረግ ለየትኛውም አካል አይቅምም ብለዋል፡፡
“የግድቡ ድርድር ይቀጥላል” የሚል እምነት እንዳላቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡