በመንግስትና ህወሓት መካከል የሚደረገው ድርድር ሁሉንም ያሳተፈ ኢንዲሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ጠየቀ
ምክር ቤቱ፤ “የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሳይወጡ ቆይተዋል” ብሏል
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት የሚከታተል ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የኢፌዴሪ መንግስት እና ህወሓት ድርድር ሂደት ላይ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ አስታወቀ።
ሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታንን ምክር ቤቱ ሚናን በተመለከተ ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ፤ ምክር ቤቱ የሀገሪቱ ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተልና ይበጃሉ ያላቸውን ሃሳቦች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ በሰሜኑ የሀገሪቱን ክፍል የተከሰተውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የኢፌዴሪ መንግስት እና ህወሓት ለድርድር ያሳዩት ተነሳሽነት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያመሰግናል ብለዋል።
ሁለቱም ወገኖች በድርድር ሂደቱ ላይ በቅን ልቦና እንዲሳተፉ ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ምክር ቤት ለሂደቱ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አሁን የተጀመረውን ጉዳዩን በሰላም የመፍታት ተነሳሽነት ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ የገለፁ ሲሆን፤ ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን የሰላም ድርድር ሂደቱ ሁሉንም ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያሳተፈ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ይህም የሰላም ድርድር ሂደቱ ቅቡልነት እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ውጤቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንዲችል ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጋል ብለዋል።
ምክር ቤቱ፤ እንደ “ሀገራዊ ምክክር” በመሳሰሉ ቁልፍ ሀገራዊ አጅንዳዎች ላይ የራሱን አስተዋጽዖ ለማበርከት እንቅስቃሴ እንደጀመረም አስታውቀዋል።
ምክር ቤቱ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት ዝግጁ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “ምክር ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰቡ የተውጣጣና ሀገራዊ የምክክር ሂደቱን የሚከታተል ወይም የ’ሪፈረንስ’ ቡድን አቋቁሟል” ብለዋል።
በሀገሪቱ ለተከሰቱት ችግሮች መፍትሄ እንዲበጅ በማድረግ በኩል ከመንግስትን ሚና ጋር በተያያዘ ምክር ቤቱ ያለውን ግምገማ የጠየቁት ዋና ዳይሬክተሩ “በጥናት ላይ ተመርኩዘን የመንግስትን ጠንካራና ደካማ ጎን ለመናገር ለጊዜው ይቸግረናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን በሀገሪቱ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙና የተወሳሰቡ ችግሮችን የመፍታት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነትና ተግባር የሚጠይቅ መሆኑም አስገንዝበዋል።
በዚህም መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እንደ ተቋም በሀገሪቱ በተከሰቱ በርካታ ችግሮች ዙሪያ የተለያዩ መግለጫዎችን በማውጣት ብቻ ሲሳተፍ እንደነበረ እና ኃላፊነቱን ለመወጣት ጥረት ሲያደረግ መቆየቱ አስታውሰዋል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሄኖክ።
ዋና ዳይሬክተሩ፤ “በሀገሪቱ ካሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንጻር የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አባል የሆኑ የሲቪለ ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ሲመዘን ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለው ያምናሉ ወይ.?” በሚል ከአል-ዐይን አማርኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ኃላፊነቱ ተወጥተዋል ለማለት እንደማይደፍሩ ተናግረዋል።
ለዚህም ለአስር አመታት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “በሰላም ጉዳይና በዴሞከራሲ ግንባታ” በመሳሰሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው በህግም ጭምር ገደብ ተጥሎ መቆየቱ በምክንያትነት አንስተዋል።
ከምክር ቤቱ እንደ አዲስ ከተቋቋመ አንድ አመት ከስድስት ወር ከመሆኑና የምክር ቤቱ ስራዎች ጊዜ የሚፈልጉ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ እየተወጣ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይገጥማቸው የነበረውን “የፋይናንስ እጥረት” ጋር ተያይዞ ከአል-ዐይን አማርኛ ለቀረበላቸው ጥያቄም ዋና ዳይሬክተሩ “አዎ የፋይናስ ክፍተት አይኖራል፤ ለስራዎቻችን ፋይናንስ ወሳኝ መሆኑም እናምናለን፤ ነገር ግን አሁን ስራዎቻችን ያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉልን ነው፤ ቢያንስ አሁን ያቀድናቸው ስራዎች ለመስራት እንችላልን የሚል ተስፋ አለን” ብለዋል።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በሪፎርም ከተመሰረቱ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አንዱ መሆኑ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የህግ ማሻሻያም ጭምር በማድረግ ምክር ቤቱ በአደረጃጀት እና አሰራሮችን ግንባታ ስራዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራ መሆንም አክለው ገልጸዋል።
ከተመሰረተ አንድ ዓመት ከስድስት ወር የሆነው እና ከስሩ አራት ሺህ የሚደርሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የያዘው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።