የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳር ጫና ውስጥ ገብቷል ተባለ
ለስምንት ቀናት በኦሮሚያ ፖሊስ የታሰሩት የኢሰመጉ ሰራተኞች በዋስትና ተለቀዋል
እስሩ ባለሞያዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ እንቅፋት ለመሆንና ለማሸማቀቅ የተደረገ ነው ብሏል ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አራት ሰራተኞች በኦሮሚያ ክልል ከስምንት ቀናት እስር በኋላ በዋስ ተፈተዋል።
የድርጅቲ ሦስት መርማሪዎችና አንድ ጉዳይ አስፈጻሚና ሹፌር ዓለም ገና አካባቢ ቤታቸው የፈረሰባቸውን ሰዎች ጉዳይ በመመርመር ላይ እያሉ ታህሳስ 27፤ 2015 ዓ.ም. አዲስ በተመሰረተው ሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ጉዳ ክፍለ ከተማ በፖሲስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ፖሊስ ‘ያለ ፈቃድ ስራ ሰርታችኋል፣ ፎቶ አንስታችኋልና ቤት ማፍረሱ ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው ብላችኋል’ በሚል ሰራተኞችን በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የኢሰመጉ ኃላፊ ዳን ይርጋ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ወንጀል ሳይሰሩ ሰራተኞቹ መታሰራቸው እንዳሳዘነው የጠቀሰው ኢሰመጉ፤ ሰራተኞቹ ሊያዙ የሚችሉበት ምንም አግባብ የለም ብሏል። ይህንም ስናስረዳ ነበር የሚሉት ኃላፊው ሰራተኞቹ ከሳምንት በላይ ታስረው ጥር 04 በአራት ሽህና በሦስት ሽህ ብር ዋስትና ተለቀዋል ብለዋል።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የሆነ ህጋዊ ተቋም ስራውን ለመስራት ፖሊስን ማሳወቅ አይጠበቅበትም ያሉት ዳን ይረርጋ፤ ሰራተኞቹ ማንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ መሳየታቸውን ተናግረዋል።
ሰራተኞቹ በፍርድ ቤት ሦስት ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፤ የትብብር ደብዳቤ ባለመያዝ፣ ፈቃድ ሳይጠይቁ በመመርመርና ፎቶ ግራፍ በማንሳት ተከሰዋል። የኢሰመጉ ኃላፊ ክሶቹ ለማሳሰር የሚያበቁ አይደሉም ብለዋል።
“ከታሰሩ በኋላም ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም ብለን መልስ ስንሰጥ ነበር። ለምሳሌ ባለሞያዎቹ መታወቂያ ይዘዋል፣ ጉዳዩንም በደንብ ማስረዳት የሚችሉ ናቸው። ፎቶ ማንሳት ደግሞ የምርመራ ማስረጃ ነው። ፈቃድ መጠየቅ፣ የትብብር ደብዳሜ መያዝና ፎቶ ማንሳት እነሱን [ባለሞያዎቹን] ለማሰር ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
ኢሰመጉ ድርጊቱ ባለሞያዎቹ በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ እንቅፋት ለመሆንና ለማሸማቀቅ የተደረገ መሆኑን ተናግሯል።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ሰራተኞች መታሰር አንደምታው የሲቪክ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን ያሳያል ተብሏል።
የኢሰመጉ ሰራተኞች መታሰርን በሚመለከት 12 የሚደርሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፤ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫናዎች ምህዳሩ ላይ የማይገባ አሻራ እያሳረፉ ነው ብለዋል።
በጋራ መግለጫቸው ድርጅቶቹ መንግስት ኢትዮጵያ ለፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነት የህገ-መንግስቷ አካል በመሆናቸው ጥብቅና ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።
የዘፈቀደ እስራቱን የፈጸሙት የመንግስት አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑም ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።
እስሩ በኢሰመጉ ባለሞያዎች ላይ ይፈጸም እንጂ ተጽዕኖው ለሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችና ለመብት ተሟጋቾች እንደሚተርፍ ዳን ይርጋ ተናግረዋል። በተለይም ነጻና ገለልተኛ ሆነው ለሚሰሩ ተሟጋቾች መልዕክቱ ከባድ መሆኑንም ያነሳሉ።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳር አፋኝ ነበር የሚባለው አዋጅን ከማሻሻል ጀምሮ ተወሰዱ እርምጃዎች ተስፋ ሰጭ እንደሆኑ ይነሳል። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ተስፋ እየጨለመ መሆኑን ተሟጋቾች የሚደርሱ ጫናዎችን በመጥቀስ ይናገራሉ።
የኢሰመጉ ኃላፊ ዳን ይርጋ “ህገ-ወጥ እስር” ባሉት ሰሞነኛ ድርጊት በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ላይ ለተሰማሩትም ሆነ ለመሰማራት ፍላጎት ያላችው አካላትን ጥቃት ላይ የሚጥል ከባቢ እንዳለ የሚያሳይ ነው ይላሉ።
“የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳር ጫና ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው። ዘርፉ ምን ያህል ጫና ላይ እንዳለ ያሳይል። አራት ሰራተኞችን ለስምንት ቀን ማሰር ቀላል አይደለም።
ጉዳዩን በአግባቡ ለማስረዳት እየጣርን በነበረበት ሰዓት እንደዚህ አይነት እስር መፈጸሙ ሲቪል ማህበረሰብ ምህዳር ላይ እንደሚሰራ ተቋም ስራችን ላይ ጫና ተጋርጦብናል።
ምንም ጥያቄ የለውም። የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳሩ ጫና እየተፈጠረ እንደሆነ ለማየት ብዙ ገጽ ማገላበት አያስፈልግም። የመጀመሪያው ገጽ ላይ ማየት ይቻላል” ብለዋል።
ኃላፊው ሰብዓዊ መብትን የማስከበር የአንበሳው ኃላፊነት የተጣለበት መንግስት ለስራችን እገዛ እንጂ ጫና ማድረግ አልነበትም ይላሉ። መንግስት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲጠብቅ የስራችን ጥቅም በቀላሉ ሊታይ አይገባም ሲሉም አክለዋል።
“የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት እንዲያገኙ፣ እንዲታረሙ፣ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ፣ የተጎዱት እንዲካሱ እንዲሁም ወደ ፊት ደግሞ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ አስተማሪ የሚሆኑ ሪፖርቶችን ነው የምናወጣው። ይሄ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳሩ በቂ ትኩረት፣ ችግሩን በሚመጥን መልኩ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉም ጠይቀዋል።
መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማስከበር ግዴታውን እንዲወጣም አደራ ተብሏል።