ከሶስት የአረብ ሀገራት የተውጣጡ 40ሺ ታጣቂዎች ሄዝቦላን ለመቀላቀል ጎላን ሀይት አቅራቢያ መድረሳቸው ተዘገበ
የእስራኤል የጦሩ ምንም እንኳን ተዋጊዎቹ የሰለጠኑ ባይሆኑም እንደሚያሳስበው ገልጿል
ደማስቆ፣ ሄዝቦላ እና ቴልአቪቭ እስካሁን ሪፖርቱን በተመለከተ በይፋ ያሉት ነገር የለም
ከሶሰት የአረብ ሀገራት የተውጣጡ 40ሺ ታጣቂዎች ሄዝቦላን ለመቀላቀል ጎላን ሀይት አቅራቢያ መድረሳቸው ተዘገበ።
ከሶስት የአረብ ሀራት የተውጣጡ ቁጥራቸው 40ሺ የሚሆኑ ሚሊሻዎች እና ቅጥረኛ ተዋጊዎች ከሄዝቦላ ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት በእስራኤል በተያዘው ጎላን ሀይት አቅራቢያ መድረሳቸውን ሀርቴዝ የተባለውን የእስራኤል እለታዊ ጋዜጣ የትናንት እትም ጠቅሰው በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የእስራኤል ጦር ከባለፈው ሰኞ ጠዋት ጀምሮ በሊባኖስ ላይ ተከታታይ የአየር ጥቃት እያደረሰ ይገኛል። በጥቃቱ 95 ሴቶችን እና 50 ህጻናትን ጨምሮ 560 ሰዎች መገደላቸውን እና ሌሎች 1835 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር ፊራስ አቢያድ ተናግረዋል።
አንደዘገባው ከሆነ ብዙ ሺ ቁጥር እንዳላቸው የተጠቀሰው እነዚህ ታጣቂዎች ከሶሪያ፣ የመን እና ኢራቅ የመጡ ናቸው።
ሀርቴዝ በስም ያልጠቀሰውን ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው "የእስራኤል ጦር ከሶሪያ፣ ከኢራቅ እና ከየመን ጨምሮ ከበርካታ ሀገራት ወደ ጎላን ሀይት አቅራቢያ መጥተው ጦርነቱን ለመቀላቀል የሄዝቦላን ዋና ጸኃፊ ነስረላህን የሚጠብቁ ቁጥራቸው 40ሺ ገደማ የሚሆኑ ታዋጊዎች እና ቅጥረኞች ጉዳይ በሰጋት እያየው ነው።"
ጦሩ ምንም እንኳን ተዋጊዎቹ የሰለጠኑ ባይሆኑም እንደሚያሳስበው ገልጿል።
"አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የእነዚህን ኃይሎች እዚህ መስፈር እንደማንፈልግ ለፕሬዝደንት በሽር አላሳድ ለማሳየት ሶሪያ ውስጥ እርምጃ ልንወስድ እንችላለን" ሲል ይኸው ጋዜጣ የምንጩን ማንነት ሳይጠቅስ ዘግቧል።
ደማስቆ፣ ሄዝቦላ እና ቴልአቪቭ እስካሁን ሪፖርቱን በተመለከተ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
እስራኤል እና ሄዝቦላ 41ሺ በላይ ፍልስጤማውያን እንዲገደሉ ምክንያት የሆነው የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ከባለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በድንበር አካባቢዎች ተኩስ እየተለዋወጡ ነው።
ነገርግን እስራኤል ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በሊባኖስ ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ያስከተለው ጉዳት ከ1975-90 ከተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት ወዲህ እጅግ ከባድ ነው ተብሏል።
አለምአቀፉ ማህበረሰብ ጦርነቱ ወደ ቀጣናው እንዳይስፋፋ ስጋቱን ቢገልጽም፣ ትኩረቴን ከጋዛ ወደ ሄዝቦላ አድርጌያለሁ ያለችው እስራኤል 1600 በላይ ኢላማዎችን ማውደሟን ገልጻለች።