40 ዓመት እድሜ ያስቆጠረው የአይነ ስውራን የሙዚቃ ባንድ “ወጋገን”
ባንዱ መጀመሪያ “ሬንቦ” በሚል በግል ደረጃ የተቋቋመ ሲሆን፤ አሁን ላይ “ወጋገን” በሚል ስያሜ እየሰራ ይገኛል
ተሾመ አሰግድ እና ይርዳው ጤናውን ጨምሮ በርካታ እውቅ ሙዚቀኞችን ማፍራት ችሏል
ከሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾች እስከ ድምጻውያን ድረስ በአይነ ስውራን ብቻ የሚሰራበት ባንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመሰረተ 40 ዓመታት ያክል አስቆጥሯል።
ባንዱ መጀመሪያ ላይ “ሬንቦ” በሚል ስያሜ ከ1968 እስከ 1972 ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ ከ1973 ዓ.ም ጀመሮ “ወጋገን” በሚል ስያሜ እስካሁን ድረስ እየሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት በህግ ማማከር እና በጥብቅና ሙያ ላይ የሚገኙት ከአይነ ስውራን ባንድ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ዘመድ ገብረአምላክ በባንዱ አመሰራረት እና ታሪክ ዙሪየ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የአይነ ስውራን ባንድ መሰረት የሰበታ መራ እውራን ትምህርት ቤት ነው ሲሉ መነሸውን የሚያስታውስት አቶ ዘመድ፤ በትምህርት ቤቱ ቆይታ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ ሙዚቃ ይሰጥ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
በትምህር ቤቱ ውስጥ የተጀመረው የሙዚቃ ፍቅር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በያሬድ ሙዚቃ ትምህር ቤት ውስጥ ሙዚቃ እስከ መለማመድ መዝለቁን የሚናገሩት አቶ ዘመድ፤ በዚያ ትምህር ቤት ውስጥ ከተሰባሰቡ ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አብሮ የመስራት ሀሳብ ተወለደ ይላሉ።
“በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦርኬስትራ ሙዚቃ ተጫዋቾችን ይፈልግ ነበረ፤ እኛም የሚያስራንን እንፈልግ ነበር” ያሉት አቶ ዘመድ፤ በዚህም ከእነ ተሸመ አሰግድ፣ እና አብዱቄ ከፈኒ ጋር በመሆን ባንዱን ተቀላቅለው ስራ መጀመራቸውን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ኦርኬስትራ ውስጥ እየሰሩ “የራሳችን ባንድ እንመስርት”በሚል የሙዚቃ መሳሪያ መግዛት መጀመራቸውን እና ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪየ ካሟሉ በኋላ 7 ሰዎች ሆነው “ሬንቦ” የአይነ ስውራን ባድን መመስረታቸውን ይናገራሉ።
ባንዱ ሙሉ በሙሉ በአይነ ስውራን ብቻ የሚመራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዘመድ፤ ይህም አይነ ስውራን በራሳቸው መስራት እንደሚችሉ ለማሳየት በማሰብ የተሰራ ነው፤ በዚህም ስኬታማ መሆን እንደሚቻል ማሳየት ተችሏል ይላሉ።
የሬን ባድ የመጀመሪያ ስራም የተሸመ አሰግድ “ባቲ እና ትዝታ” ነው ያሉት አቶ ዘመድ፤ ከዚያ በኋላ ከብዙነሽ በቀለ፣ ከክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ፣ ከታምራት ሞላ፣ ጌታመሳይ አበበ እና ከሌሎች ድምጻውያን ጋር መስራታቸውን ተናግረዋል።
ባንዱ በዚህ መልኩ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ደርግ ወደ ስልጣን በመምጣቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ፣ የእድገት በህብረት መምጣት እንዲሁመ የባንዱ አባላት ትምህርት ለመቀጣል ወደ ዩኒቨርሲቲ በመመለሳቸው ባንዱ የሙሉ ጊዜ ስራ አቁሞ በመድረክ ስራ ብቻ መቀጠሉን ይናገራሉ።
በኋላ ላይ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሄራዊ ማህበር በአነስተኛ ዋጋ በመሸጥ “ወጋገን” ባንድ እንዲደራጅ መደረጉን ተናረዋል።
ወጋገን ባድንም የቀድሞ የሬንቦ ባንድ ተጫዋቾችን ጨምሮ አዳዲስ የሙዚቃ ባለሙያዎችን በመቀለቃል ስራውን ቀጥሎ እንደነበረም አስታውቀዋል።
የወጋገን ባንድ አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ሳህሌ በበኩላቸው፤ ወጋገን ባድ የሬንቦ ባንድ መበተንን ተከትሎ በ1973 ዓ.ም በቀድሞ የሬንቦ ባንድ አባላት አማካኝነት እንደተቋቋም ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ባንዱ ከተቋቋመ ጀምሮ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቢቆይም በአሁኑ ሰዓት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ በሙሉ አቅሙ እየሰራ እንዳልሆነም ይገልጸሉ።
ሆኖም ግን ባንዱ አልፎ አልፎ የተለያዩ መድረክ ስራዎችን በበዓላት እና በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ እያቀረበ እንደሚገኝም ነው አቶ ቢኒያም የነገሩን።
ባንዱ ባለፉት 40 ዓመታ ውስጥ አንጋፋዎቹን ተሸመ አስግድን እና ይርዳው ጤናውን ጨምሮ በርካታ ድምፃውያንን ማፍራቱን የሚናገሩት አቶ ቢኒያም፤ አሁንም ቢሆን እንደ ኢትዮጵያን አይድል እና ባላገሩ ያሉ የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ላይ እስከ 10ኛ ደረጃ መውጣት የቻሉ ድምውያንን ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል።
የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶች በሚዘጋጁበት ወቅት ልክ እንደ ሌሎች የሙዚቃ ባንዶች ጥሪ ቢደረግልን በሙሉ አቅም መስራት እንችላለን ያሉት አቶ ቢኒያም፤ በዝግጅቶች ላይ ጋብዙን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።