በ1955 ዓ/ም ነበር ወደ እውቁ የሙዚቃ ባንድ ፖሊስ ኦርኬስትራ ሊቀላቀልና የሙዚቃ ህይወቱን ሊጀምር የቻለው
ብዙዎችን ሲያዝናና ሲያስደስት የኖረ ነው፡፡ በብዙዎች ልብ ውስጥ ያረፉ ስራዎችን ለመስራት ችሎም የብዙዎችን ጆሮ ለመጎተት፤ ቀልባቸውንም ለመግዛት ችሏል፡፡ ቄንጠኛና ሽቅርቅርነቱን የተመለከቱ በመድረክ እንቅስቃሴዎቹ የተደመሙ ብዙዎችም ከአሜሪካዊው የሮክ እና ሮል ንጉስ ጋር አመሳስለው “ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ” ሲሉ ጠርተውታል፡፡
ሰኔ 10 ቀን 1934 ዓ.ም በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ተስፋ ገብረ ስላሴ ማተሚያ ቤት አካባቢ ተወልዶ ያደገውን እንቁውን ኢትዮጵያዊ ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴን፡፡
ወርቃማው የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘመን ተብሎ በሚጠራው በያኔው ዘመን ለመግነን ከቻሉት እንቁ ኢትዮጵያዊ ድምጻውያን መካከል አንዱ የሆነው ዓለማየሁ ወላጅ እናቱ ወ/ሮ በላይነሽ ዮሴፍ በ2 ወሩ ወደ ደሴ ይዘውት ሄደው እስከ ሶስት ዓመቱ በዚያው አድጓል፡፡
በወቅቱ የከተማ ታክሲዎችን ያሽከረክሩ ከነበሩ ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት ወላጅ አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ ይማር ብለው ወደ አዲስ አበባ አምጥተውት የአብነት ትምህርትን አስተምረውታል፡፡ በመቀጠልም ታዳጊው ዓለማየሁ በሊሴ ገብረማርያም፣ በዑመር ሰመተር፣ በአብዮት ቅርስ እና በአርበኞች ትምህርት ቤት ተምሯል፡፡
በትምህርት ቤቱ በተለይ በአርበኞች ሲያቀርባቸው በነበሩ የሙዚቃ ስራዎቹ ከመደመም አልፈው እምቅ የሙዚቃ አቅም እንዳለው ቀድመው ለማወቅ የቻሉት ኮሎኔል ረታ ደመቀ በ1955 ዓ/ም ወደ ፖሊስ ኦርኬስትራ ጋብዘውት በዚያው እውቁን የሙዚቃ ባንድ ሊቀላቀልና የሙዚቃ ህይወቱን ሊጀምር ችሏል፡፡
ዓለማየሁ በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትን የነ ኤልቪስ ፕሪስሌይን ሮክ እና ሮል ሙዚቃዎች ይጫወት ነበር፡፡ እንቁ ተሰጥዖውን ተመልክተው የተደነቁ ብዙዎችም “ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ” የሚል ቅፅል ሰጥተውታል።
የጥላሁን ገሰሰን ዘፈኖች ይጫወት እንደነበር የሚናገረው ዓለማየሁ “ተማር ልጄ” እና “አዲስ አበባ ቤቴ” በሚሉ አይረሴ ዘፈኖቹ ይታወቃል፡፡
“ስቀሽ አታስቂኝ”፣ “ እንደ አሞራ”፣ “ ማን ይሆን ትልቅ ሰው”፣ “ምሽቱ ደመቀ”፣ “የወይን ሃረጊቱ”፣ “የሰው ቤት የሰው ነው”፣ “ደንየው ደነባ”፣ “ትማርኪያለሽ”፣ “ወልደሽ ተኪ እናቴ”፣ “ማሪኝ ፡ ብየሻለሁ”ም ከዓለማየሁ ታዋቂ ስራዎች መካከል ናቸው።
አጠቃላይ የዘፈናቸው የሙዚቃ ስራዎች ብዛት ከሶስት መቶ ሰማንያ እንደሚልቁ ከአራት ዓመታት በፊት በሸገር ኤፍ ኤም ከጨዋታ እንግዳ የሬዲዮ ፕሮግራም ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል፡፡
ዓለማየሁ ከአንጋፋው ጓደኛውና ሌላኛው ድምጻዊ ግርማ በየነ ጋር በመሆን ዓለም-ግርማ የተሰኘ የሙዚቃ ባንድን አቋቁሞ ነበር፡፡ ደርግ ስልጣን ከመያዙ በፊት በነበሩ 15 ዓመታት ውስጥም 30 ነጠላ ስራዎችን ለአድናቂዎቹ ለማድረስ ችሏል፡፡ ይህ ልክ እንደባልደረቦቹ ሁሉ ከሃገር እንዲወጣ አስገድዶት እንደነበርም ነው የህይወት ታሪኩን የተመለከቱ መረጃዎች ያመለከቱት፡፡
በአውሮፓ እና አሜሪካ በነበረው ቆይታም ዝናና እውቅናን ያስገኙለትን ስራዎች ለመስራት ችሏል፡፡ ቁንጮ የኢትዮጵያ ድምጻውያን ስራዎች “ኢትዮፒክስ” በሚል መጠሪያ ተሰባስበው በተከታታይ መታተም የመጀመሩትም በዚሁ ጊዜ ነበር፡፡
ይህም የሙዚቃ ስራዎችን ሸክላ ላይ በማሳተም በቀዳሚነት የሚጠቀሰውን ዓለማየሁን የበለጠ ለመታወቅ አስችሎታል፡፡
ዘመን ዘለል ስራዎችን ለማበርከት የቻለውን ዓለማየሁን ስለ አበርክቶው ለማመስገንና ለመሸለም በአንጋፋዋ የጥበብ ሰው በዓለምጸሃይ ወዳጆ ጣይቱ የባሕልና የትምህርት ማዕከል ውጥን ተይዞ ነበር የሚሉ መረጃዎችም ወጥተዋል፡፡
ሆኖም ይህ ታላቅ ሙዚቀኛ ትናንት ሌሊቱን፤ ለዛሬ ነሀሴ 28 ቀን 2013 ዓ/ም አጥቢያ በገጠመው ድንገተኛ ህመም ምክንያት ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ተሰምቷል፡፡
በህልፈተ ህይወቱ ማዘኑን የገለጸው እውቁ የሙዚቃ መምህር እና ሊቅ ሰርጸ ፍሬ ስብሐት
“በኢትዮጵያ ሙዚቃ የሬኮርዲንግ ታሪክ ውስጥ የተሣኩ እና ጥራታቸው ከፍ ያሉ ከ400 በላይ ምርጥ ሥራዎችን ያበረከተው ዓለማየሁ እሸቴ፣ "ጌሪ ኮፐር"፣"ኢትዮጵያዊው ኧልቪስ"፣ "ዓለማየሁ ቴክሱ፣ ነጭ ነው ፈረሱ" እየተባለ በአድማጮቹ የአድናቆት ቅጽሎች የተወደሰው ዓለማየሁ እሸቴ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ዓለም አቀፍ ተወዳጅነት እንዲያገኝ ያደረገ ድንቅ ድምፃዊ ነበር” ሲል በማህበራዊ ገጹ አስፍሯል።
“ወርቃማው” እየተባለ ለሚጠቀሰው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘመን፣ የመጀመሪያው ተጠቃሽ ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ እንደነበርም ነው ሰርጸ ያሰፈረው።
ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በአንጋፋው ድምጻዊ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡