ምርጫ ቦርድ በ2015ዓ.ም ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች አካባቢያዊ ምርጫ እንደሚያካሂድ ገለጸ
በጸጥታ ምክንያት ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች ከአካባቢያዊ ምርጫው ጋር በቅንጅት ሊካሄድ ይችላል ብሏል ቦርዱ
በኢትዮጵያ አካባቢያዊ ምርጫ ከተካሄደ 10 ዓመት ሆኖታል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ2015ዓ.ም ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎች አካባቢያዊ ምርጫ እንደሚያካሂድ ገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው በተያዘው 2015 ዓ.ም የአካባቢያዊ ምርጫ ይካሄዳል፡፡ቦርዱ ይህን ያስታወቀው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአካባቢያዊ ምርጫ ዙሪያ ወይይት ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በመድረኩ ላይ እንዳሉት "ቦርዱ በያዝነው በጀት ዓመት ከትግራይ ክልል ውጪ አካባቢያዊ ምርጫ ለማካሄድ አቅዷል" ብለዋል።
ይሁንና አካባቢያዊ ምርጫው መቼ ይካሄዳል በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ " አካባቢያዊ ምርጫ ሰፊ የሰው ሀይል እና በጀት ስለሚጠይቅ እንዲሁም የክልሎች ሁኔታ ከቦታ ቦታ ስለሚለያይ አካባቢያዊ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን በዚህ ቀን ማለት አይቻልም፣ በሁሉም ቦታዎች በተመሳሳይ ቀን ሊካሄድ አይችልም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሰብሳቢዋ "ጠቅላላ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች የጸትታ ሁኔታው ከተስተካከለ” ምርጫው እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ከአካባቢያዊ ምርጫው ጋር አንድ ላይ ይደረግ ወይስ አይደረግም የሚለው ተጨማሪ ውይይት እና ውሳኔ ያስፈልገዋል" ሲሉም ስራ አስፈጻሚዋ አክለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ አዳዲስ ወጣቶችን እንዲያሳትፉ እናበረታታለን ያሉት ወይዘሪት ብርቱካን ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት መጀመሩን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አካባቢያዊ ምርጫ ከተካሄደ 10 ዓመት የሞላው ሲሆን ከዚህ በፊት ከጠቅላላው ምርጫ ጋር መካሄዱ መራጮችን ያሳስታል በሚል ለብቻ እንዲካሄድ መወሰኑ ይታወሳል።
አካባቢያዊ ምርጫ ማለት ዜጎች በቀበሌ፣ ወረዳ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ በልዩ ዞን ምክር ቤቶች የሚወክሏቸውን የህዝብ ወኪሎች የሚመረጡበት የምርጫ ስርዓት ነው።
በኢትዮጵያ፤ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በትግራይ ጠቅላላ መርጫው ሳይካሄድ ቀርቷል፤ የማሟያ ምርጫው አይካሄድም፡፡
በድርድር ይፈታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ግጭት በድጋሚ ሊያገረሽ አገርሽቷል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የነበረው ግጭት ለወራት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ከሁለት ሳምንት በድጋሚ ተቀስቅሷል።
የፌደራል መንግስት ህወሓት የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጥቃት መክፈቱን እና ጥቃቱን እንደሚመክትም መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአማራ ክልል በሰቆጣ፣በወልዲያ፣ በደሴ እና በከምቦልቻ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰጋት የሰአት እለፊ ገደብ ተጥሏል።
ሁለቱም አካለት ለወራት የዘለቀውን የተናጠል ተኩስ አቁም በመጣስ አንደኛው ሌላኛውን በመወንጀል ላይ ናቸው።
ግጭቱን በድርድር ለመቋጨት ሁለቱም አካላት በተናጠል ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም ዳግም ወደ ግጭት ገብተዋል። የአፍሪካ ህብረት ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ሁቱንም አካላት በተደጋጋሚ ያገኘ ቢሆንም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላመጣም።
ህወሓት ለመደራደር ያለውን ዝግጁነት የገለጸ ሲሆን በህብረቱ ላይ ግን የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል።