የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከቁም እስር እንዲለቀቁ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ
ቦርዱ አቶ ዳውድ በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር ስርመሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል
አቶ ዳውድ ኢብሳ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከቁም እስር እንዲለቀቁ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ።
ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው የምክክር መድረክ ላይ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የማጣራት ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልጿል።
በዚህም የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር ላይ ናቸው የሚል ጥቆማ በደረሰው መሰረት በተለያዩ መንገዶች ማጣራቱን አስታውቋል።
የቦርዱ መርማሪ አካላት በአቶ ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤት በማምራት ሊቀመንበሩን ለማግኘት ባደረገው ማጣራት አቶ ዳውድ ኢብሳ በቁም እስር ላይ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህም መሰረት ቦርዱ የላካቸው አጣሪዎች በአቶ ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ ሲቪል የለበሱ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እንደተቀበሏቸው እና አቶ ዳውድ ኢብሳን ለማግኘት የግድ ፈቃድ እንደሚያስፈልጋቸው መታዘዛቸውንም የቦርዱ መግለጫ ላይ ተገልጿል።
በመሆኑም አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 2013 ዓ..ም ጀምሮ በመኖሪያ ቤታቸው በቁም እስር ላይ መሆናቸውን ከራሳቸው ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ማረጋገጡን ቦርዱ አስታውቋል።
ቦርዱ ይህ አግባብነት እንደሌለው በማሳወቅ እስሩ በአፋጣኝ እንዲቆም ያሳሰበ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የመደቡትን ጥበቃ አንስተው የአቶ ዳውድ ኢብሳን የመንቀሳቀስ መብት በአስቸኳይ እንዲያስከብሩና ይህንንም እንዲያሳውቁት አስጠንቅቋል።