የሶማሊያ ጦር በምስራቅ በኩል 700 ኪሜ.፣በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሜ. የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ ነበር
የሶማሊያ ጦር በምስራቅ በኩል 700 ኪሜ.፣በደቡብ በኩል ደግሞ 300 ኪሜ. የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ ነበር
ከዛሬ 42 ዓመታት በፊት የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር ድንበር ጥሶ ወደ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ገብቶ የነበረውን የሶማሊያን ሰራዊት ከኢትዮጵያ ግዛት በማስወጣት ካራማራ ተራራ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማወለብለቡን ታሪክ ያስታውሳል፡፡
የካራማራ ድል ከደርግ ውድቀት በኋላ በመንግስት ደረጃ የማይከበር ድል ቢሆንም የቀድሞ ሰራዊት አባላትና ግለሰቦች በተነሳሽነት እያከበሩት ነው፤ በዓሉም ብሄራዊ በዓል ሆኖ በመንግስት እንዲከበር ይፈልጋሉ፡፡
ሶማሊያ በ1952 ዓ.ም ከጣሊያንና ከእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ነፃነቷን ባገኘች ማግሥት የሀገሪቱ መሪዎች “ታላቋ ሶማሊያን እንገነባለን” የሚል ህልም ማለም ጀመሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በ1953 ዓ.ም የድንበር ላይ ትንኮሳ ጀምረው በ1956 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር አብድረሺ አሊ ሸርማርኬ እንዲሁም በ1969፣ በ1972 እና በ1973 ዓ.ም ደግሞ ፕሬዝደንት ዚያድ ባሬ (ሜጀር ጀኔራል) የሶማሊያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ እንዲገባና ወረራ እንዲፈፅም ሰራዊታቸውን አዘዙ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ደግሞ ሰርጎ ገቦችን አስታጥቆ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በማስገባት ፈንጅ በማፈንዳት፣ ድንገተኛና የደፈጣ ጥቃቶችን በመፈፀም እንዲሁም ባለስልጣናትንና ሰላማዊ ሰዎችን አፍኖ በመውሰድ ለኢትዮጵያ ሰላምና ልማት መሰናክል ሆነው መቆየታቸውንም በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ የሶማሊያ ወረራዎችና ጥቃቶች በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢመለሱም ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን አለመቻሉ ይገለጻል፡፡ በተለይ የ1969 ዓ.ም የዚያድ ባሬ ወረራ የኢትዮጵያ ድንበር በምስራቅ በኩል እስከ 700 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በደቡብ በኩል ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ሜትር በሶማሊያ ሰራዊት እንዲደፈር፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን እንዲሞቱና እንዲቆስሉ፣ አካል ጉዳተኛ እንዲሆኑ በአጠቃላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በርካታ የሕይወትና የንብረት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ያደረገ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በወቅቱ በብዙ የውስጥ ችግሮች (የመሐል አገር የሥልጣን ሽኩቻ፣ የነጻነት ጠያቂዎች በሃገር ቤት፣ የተለመደው ድህነትና ረሀብ …) ተወጥራ ስለነበር የዚያድ ባሬ ወረራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባት ነበር ይላሉ የታሪክ ጸሐፊያን፡፡
ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር ሰፊ የሰው ኃይል፣ የትጥቅ፣ የስንቅ፣ የሥነ ልቦና ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች፤ኢትዮጵያ ግን በውስጣዊ ችግሮች ከመወጠሯም ባሻገር በወቅቱ የነበራት የሰራዊት ቁጥርና ጥራትእንዲሁም የትጥቅ አቅርቦት እጅግ የተመናመነ እንደነበርም ነው የሚገለጸው፡፡
300ሺ የሚሆን ሕዝባዊ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ ለውጊያ የተሰለፈ ሲሆን ፤የኩባና የደቡብ የመን መንግሥታት ጦራቸውን ይዘው ከኢትዮጵያ ጎን መሰለፋቸውም ይታወሳል፡፡ ሶቭየት ኅብረት በጀኔራል ፔትሮቭ የሚመሩ ወታደራዊ አማካሪዎቿን ለኢትዮጵያ ረዳት አድርጋ ወደ ኢትዮጵያ መላኳንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል ተሰልፈው ህይወታቸውን ላጡ ኩባውያ ወታደሮች በአዲስ አባበ መታሰቢያ ተሰርቶላቸዋል፡፡
የሶማሊያን ሰራዊት ከኢትዮጵያ ግዛት የማባረሩ ዘመቻ በሐምሌ ወር 1969 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ ኢትዮጵያውያን በምድርና በአየር አስደናቂ ገድል ስለመፈጸማቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ተናግረዋል፡፡ ዘመቻው እስከ የካቲት ወር 1970 ዓ.ም ቆይቶ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያ ሰራዊት ተከቦ መፈናፈኛ ሲያጣ ለአሜሪካና ለሶቭየት ኅብረት የድረሱልኝ ጩኸቱን አሰማ፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰራዊት የሶማሊያን ጦር እያባረረ የሶማሊያን ድንበር ጥሶ ወደ ሃርጌሳ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት ስለነበር ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው የነበሩት የውጭ አገራት የኢትዮጵያ ጦር ወደ ሶማሊያ ግዛት እንዳይገባ ልመናና ተማፅኖ ጭምር ማቅረብ ጀመሩ፡፡
አሜሪካና ሶቭየት ኅብረትም ኢትዮጵያና ሶማሊያ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ፤የኢትዮጵያ ሰራዊት ወደ ሶማሊያ ድንበር ጥሶ እንዳይገባና የሶማሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ድንበር በ24 ሰዓታት ውስጥ ጠቅልሎ እንዲወጣ ጥሪ አቀረቡ፡፡ የአሜሪካና የሶቭየት ኅብረት ጥሪ ተፈፃሚ ሆነ፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊትም የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም ካራማራ ተራራ ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውለበለበ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ የድል ዕለት ታዲያ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው አይደለም የሚሉ ወቀሳዎች አሉ፡፡በተለይ ዕለቱን ሳይቀር ብዙዎች የማያስታውሱት እንደሆነና መንግስትም ሰፊ ትኩረት እየሰጠው እንዳልሆነ ይነገራል፡፡
በወቅቱ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የኢትዮጵያ ወታደራዊ መሪዎች ሳይቀሩ እየተዘከሩና እየታወሱ አለመሆኑም ይገለጻል፡፡ 42ኛው የካራማራ ድል በቀድሞው የሰራዊት መሪዎችና አባላት፣ የኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት ማህበር እንዲሁም ግለሰቦች በግል ተነሳሽነት አክብረውታል፡፡