3ኛው ዙር የ8100 A የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ
3ኛው ዙር የ8100 A የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ዛሬ በይፋ ተጀመረ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት 9 ዓመታት ከህብረተሰቡ 13.8 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
በዚህ ዓመት ደግሞ እስካሁን 400 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት መረጃ ያሳያል፡፡
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “የግድቡ መሃንዲስ እኛው፣… የፋይናንስ ምንጮችም እኛው” ባሉት መሰረት ሀገሪቱ ግድቡን በራሷ አቅም መገንባቷን ቀጥላለች፡፡
ዛሬ 3ኛውን ዙር የ8100 A የሕዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በይፋ ያስጀመሩት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ሁላችንም በስስት የምንጠብቀው ነው ያሉትን የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ከግብ ለማድረስ መላው ኢትዮጵያውያን እስካሁን የሚያደርጉትን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ 8100 A በመላክ መርሀ-ግብሩን ሲያስጀምሩ
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በታዛቢነት ገብተው ጫና ለማሳደር የሚያደርጉትን ሩጫ ኢትዮጵያ አትቀበልም ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ የኢትዮጵያ መንግስትም ተገቢውን ምላሽ በየጊዜው በመስጠት ላይ መሆኑን አውስተዋል፡፡
“እስካሁን መላው ኢትዮጵያውያን ባደርጉት ድጋፍ ከዓለም ግዙፍ ግድቦች አንዱን ልንጨርስ እየተቃረብን ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ተናግረዋል፡፡
“የተፈጥሮ ሀብታችንን ዓለማቀፍ መርህን መሰረት አድርገን መጠቀም መብታችን ነው” ያሉም ሲሆን ከ30 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በጨለማ ህይወታቸውን እየመሩ፣ ግድቡን እንዳንሰራ ድጋፍ አለማድረጋቸው እና ብድር መከልከላችን ሳያንስ ሌላ ጫና ማሳደር ፍርደ ገምድል ነው ሲሉ የአሜሪካን አቋም ተችተዋል፡፡
መላው ኢትዮጵያውያን አሁንም በርብርብ የቀረውን ስራ ለመጨረስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
“የአድዋ ወኔ ለግድቡ ስንቃችን ነው” በማለት ኢትዮጵያውያን ለግንባታው መጠናቀቅ ያለንንን ቁርጠኝነት፣ በ3ኛው ዙር የ8100A የገቢ ማሰባሰቢያ እንደቀድሞው ሁሉ ተሳትፎአችንን አጠናክረን በመቀጠል ልናሳይ ይገባልም ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ፅ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገ/ስላሴ 3ኛው ዙር የግድቡ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር የህብረተሰቡን የባለቤትነት ስሜት ይበልጥ ለማጎልበት በህዝብ ጥያቄ መሰረት መጀመሩን ለአል-ዐይን ተናግረዋል፡፡
በገቢ ማሰባሰቢያው ከ20 ሚሊዮኝ ብር በላይ ለማሰባሰብ መታቀዱንም ነው የገለጹት፡፡
ህብረተሰቡ ድጋፉን በማጠናከር የአሜሪካ እና የዓለም ባንክን ተጽእኖ በመቀልበስ ለሀገሩ ታሪክ እንዲሰራም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
“የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ አድዋችን ነው” ያለችው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ ደግሞ “አባይን እንዳንጠቀም ጥረት ማድረግ ማለት በደጅህ የሚያልፍ ዉሃን መጠጣት አትችልም፤ ካንተ በታች ያለው ጎረቤትህ ብቻ ይጠጣው እንደማለት ነው” ስትል የአሜሪካን በኢትዮጵያ ላይ ጫና የማድረግ ጥረት ተቃውማለች፡፡
ብቻዬን ልጠቀም የሚል ፍልስፍና በዚህ ዘመን አያዋጣም የምትለው ደራርቱ የውሀው ምንጭ የሆንን ኢትዮጵያውያን እንኳን ይሄን መሰል ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ አላራመድንም ስትል የግብጽን አቋምም ተችታለች፡፡
በመሆኑም ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን ለሁሉም ወገን የሚጠቅም በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚሁ መርህ መሰረት የግድቡን ግንባታ ከሌሎች ጉዳዮቿ በላይ ትኩረት ሰጥታ ልታከናውን ይገባል ስትልም ተናግራለች፡፡
ግምባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን ግድብ ከግብ ለማድረስ መላው ኢትዮጵያውያን አንድነታችንን እና ሰላማችንን ጠብቀን አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ልናደርግ ይገባልም ብላለች፡፡
እንደ ደራርቱ ሁሉ በአባይ ወንዝ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ አቋም ማራመድ አለበት ያለችው ደራሲ እምወድሽ በቀለም ለዚህ ደግሞ የኪነጥበቡ ዓለም ሰዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብላለች፡፡
በግብጽ አባይ/ናይል ለግብጽ የፈጣሪ ስጦታ ነው በሚል ዜጎች ከህጻንነታቸው ጀምሮ እየተማሩ እንደሚያድጉ ያነሳችው እምወድሽ ይሄም ግብጻውያን በወንዙ ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ከማድረጉም ባለፈ ወንዙ የግብጽ ብቻ ሀብት እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል ባይ ነች፡፡
ለኢትዮጵያም ቢሆን ወንዙ የፈጣሪ ችሮታ በመሆኑ፣ ወንዙን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ስለመጠቀም ዜጎች የጸና የጋራ አቋም ሊኖራቸው ይገባል በማለት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ርብርብ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቃለች፡፡
የግድቡ የውሀ ሙሌት በቀጣይ የክረምት ወራት እንደሚጀመር እና የሙከራ ኃይል ማመንጨት ደግሞ ከዓመት በኋላ በመጋቢት ወር ተግባራዊ እንደሚሆን የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ ትናንት የካቲት 24 መግለጻቸው ይታወቃል፡፡
አጠቃላይ የግድቡ ግንባታ ደግሞ ከሶስት ዓመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ መንግስት ማሳወቁ ይታወሳል፡፡