አድዋ ግድቡን ለተመለከቱ የድርድር እና የስምምነት ሂደቶች ምን ያስተምራል?
አድዋ ግድቡን ለተመለከቱ የድርድር እና የስምምነት ሂደቶች ምን ያስተምራል?
ታሪካዊ ክስተት ስለመሆኑ የሚነገርለት የአድዋ ጦርነት በውል ስምምነት የትርጉም ልዩነት ምክንያት እንደመጣ ይነገራል፡፡
በ1882 ዓ.ም ጥቅምት ወር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሱት አፄ ምኒልክ ንግስናቸውን ተከትሎ ከጣልያን መንግስት ጋር በውጫሌ ያደረጉት ስምምነት ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል፡፡
ይስማ ንጉስ ተብሎ በሚጠራ ልዩ ስፍራ የተፈረመውና በአማርኛ እና በጣልያንኛ የተጻፉ 20 አንቀጾችን የያዘው ይህ ስምምነት በ17ኛ አንቀጹ ይዞት የነበረው የጣልያንኛ ሃሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ልዕልና የሚዳፈር ብቻም ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን የሚነካ ሆኖ በመገኘቱም ነው የካቲት 23 1888 ዓ/ም ወደተካሄደው የአድዋ ጦርነት ለመግባት ግድ ያለው፡፡
እውቁ የታሪክ ምሁርና ተመራማሪ አህመድ ዘካሪያ (ፕ/ር) ስምምነቱ እንዲስተካከልና አንቀጾቹም እንዲታረሙ ኢትዮጵያ ደጋግማ ብትጠይቅም ቅኝ የመግዛት ሳይሆን ሞግዚት የመሆን (protectorate) ፍላጎት አድሮበት የነበረው ወራሪው የፋሽስት ኃይል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ጦርነት ተገብቷል ይላሉ፡፡
በወቅቱ በቅኝ ገዢነት በሰከሩ አውሮፓውያን ዘንድ በነበረው የታይታ ፍላጎት ሳቢያ አንድም እጅ ላለመስጠት ሁለትም እልህ በመጋባት ምክንያት ፋሽስት ጥያቄውን ለመቀበል አቅማምቷል፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ስምምነቶች ሳቢያ ዓይነተ ብዙ ፈተናዎችን አስተናግዳለች የሚሉት ምሁሩ ለዚህም እ.ኤ.አ ሰኔ 3 ቀን 1884 ከተፈረመው የህይወት ስምምነት (Hewett Treaty) ጀምሮ ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት እስከተፈረመው የአልጀርስ ስምምነት ያነሳሉ፡፡
በአጼ ዮሃንስ ዘመነ መንግስት በተፈረመው የህይወት ስምምነት ሳቢያ ጣሊያን በአሉላ አባ ነጋ ዶጋሊ ላይ ዶጋመድ ለመሆን ተገዷል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በቅድመ አድዋ በወራሪው ፋሺስት ጣሊያን ላይ የተቀዳጀችው ድል ነበረ፡፡
የቅርብ የሚባለው የአልጀርስ ስምምነትም አስር ሺዎች ለተቀጠፉበት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የቅርብ መነሻ ምክንያት ነው፡፡
ላለፉት 30 እና ከዚያ በላይ ዓመታት በውሃና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያገለገሉት አቶ ፈቂ አህመድ ነጋሽም ኢትዮጵያ በስምምነቶች ሳቢያ ፈተናዎችን አስተናግዳለች በሚለው በዚሁ ሃሳብ ይስማማሉ፡፡
ተስፋፊ የጎረቤት ሃገራትና ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ ቀንድ በመገኘቷ፣በቀይ ባህር የግዛት ባለቤትነቷ ኢትዮጵያን ሲያተራምሱ ኖረዋል የሚሉት ባለሙያው ለአድዋ ጦርነት በምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ የአባይ ውሃ ስለመሆኑም ይገልጻሉ፡፡
86 በመቶው ከኢትዮጵያ የሚገኘው የአባይ ወንዝ ጠላት ለሚቆሰቁሰውና ዘመናትን ለተሻገረ የእርበርስ ግጭት ምክንያት ነው የሚሉት ባለሙያው ከውጫሌ ስምምነት በፊት ወንዙን ለመጠቀም በማሰብ በጣሊያን እና ብሪታኒያ መካከል የተደረጉ የተለያዩ ስምምነቶች እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡
ብሪታኒያ ፋሽስት ወደ ደጋማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲስፋፋ የመፍቀዷ ሚስጥርም ይኸው ነው እንደባለሙያው ገለጻ፡፡
በድህረ አድዋ ከድሉ 6 ዓመታት በኋላ ብሪታኒያ ኢትዮጵያ በአባይ፣ጣና እና ሶባት ወንዝ ላይ ያለ እሷ እውቅና ውጭ ምንም ማድረግ እንዳትችል የሚያስገድድ ስምምነት አድርጋ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡
ሆኖም የመላው ጥቁር ህዝብ ድል እንደሆነ ተደርጎ በሚወሰደው አድዋ ይህን ሁሉ ፉርሽ አድርጓል፡፡
አንድነቷ የጠነከረ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት ተችሏል፡፡ የሃገረ መንግስት መገንቢያ ማገር ተደርጎም ይወሰዳል፡፡ ለሰው ልጆች ክብርና ልዕልናም ፈር ተቀዷል በአድዋ፡፡
ከዚህ ማጭበርበር በተጫናቸው የቅኝግዛት የስምምነት አንቀጾች ምክንያት ከተገኘው ድል ግድቡን ለተመለከቱ የድርድር እና የስምምነት ሂደቶች የሚጠቅሙ ብዙ ቁምነገሮችን ለመማር ይቻላል፡፡
የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር) በ124ኛው የአድዋ ድል በዓል የአከባበር ስነ ስርዓት ያደረጉት ንግግርም ይህንኑ የሚያጠይቅ፤ በስምምነቶች ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚያሳስብ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
አድዋ ለግድቡ ድርድር የመማሪያ ገጽ
የአባይ ጉዳይ ከ600 ዓመታት በፊት ጀምሮ ችግር መሆኑን የሚናገሩት ፕ/ር አህመድ ግብጽ ኢትዮጵያን በማዳከም ለመጉዳት እና ውሃን እንዳትጠቀም ለማድረግ ያልታታረችበት ጊዜ የለም ይላሉ፡፡
የተለያዩ ቡድኖችን በመደገፍ ለማጋጨት ያልሞከረችበት ጊዜም አልነበረም፡፡ በተለይም ባለፉት መቶ ዓመታት ይህ ጎልቶ የተስተዋለ ጉዳይ ነው እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፡፡
በተፋሰሱ ሃገራት የተፈረመውን የስምምነት ማዕቀፍ ሁሉም ቀድሞ እንዲፈርሙት ማድረጉ ይበጅ እንደነበር የሚናገሩት ተመራማሪው አሁንም በድርድሩ ሂደት ጥንቃቄን ማከሉ ከማዕበሉ ይታደጋል ይላሉ፡፡
በታዛቢነት ስም ወደ ድርድሩ ሂደት የገባችው አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪ ሆና መታየቷ በመካከለኛ ምስራቅ ያላትን ፍላጎት ለማሳካት ከማሰብም በላይ በካምፕ ዴቪድ ስምምነት በኩል የእስራዔልን ጥቅም የማስጠበቅ ግብ ሊኖረው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ካምፕ ዴቪድ እ.ኤ.አ በ1978 በእስራዔልና ግብጽ መካከል መፈጸሙ የሚታወስ ነው፡፡
ስለሆነም ኢትዮጵያን ከጫና ሊያወጣት እና ሊታደጋት የሚችለው ነገር ኃይል ማመንጨት መጀመሩ እንደሆነ ይናገራሉ፤ልክ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እንዳደረጉት ሁሉ ድምጽ ማሰማቱ እንደማይከፋ በመጠቆም፡፡
በታዛቢነት ስም ሾልካ የገባችው አሜሪካ እስከ ማሸማገል፣ማደራደር፣የድርድሩ አካል እስከመሆንና ጭራሽኑ የስምምነት ሰነዱን እስከማዘጋጀት እስከምትደርስ ዝም መባል አልነበረበትም የሚሉት አቶ ፈቂ አህመድ በበኩላቸው ግብጽ ስምምነቱን መፈረሟ አሁንም ኢትዮጵያን ለመጫን ያላትን ፍላጎትና ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የማይጠቅም ጥቅሟንም የማያስጠብቅ እንደሆነ ማሳያ ነው በሚል ይገልጻሉ፡፡
በድርድሩ ሂደት ሌላ 3ኛ አካል መግባት አልነበረበትም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው ብለው እንደሚያምኑ የሚናገሩት ባለሙያው አድዋ ለሉዓላዊነታችን ትክክለኛ ምስክር ነው ሲሉም ያስቀምጣሉ፡፡
አሁንም በኢትዮጵያ ምድር፣በኢትዮጵያ ውሃ ላይ፣በራሷ የውሃ ድርሻ ላይ የሚገነባውን ግድብ ለመታደግ ማንኛውንም መስዋዕትነት ከፍሎ ሃገራዊ አንድነትን በማጠናከር ወደፊት መጓዝ መፍትሄ እንደሆነም ነው የሚናገሩት፡፡
በእርግጥ ትናንት በአሜሪካ አቋምና በድርድሩ ሂደት ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ በኩል መግለጫን የሰጠው መንግስት ህዝብን ሳያማክር የሚፈርመውም ሆነ የሚያደርገው አንዳችም ስምምነት እንደሌለ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡