በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ የአሜሪካና የዓለም ባንክ ሚና መለየት እንዳለበት ኢትዮጵያ አሳሰበች
በህዳሴው ግድብ ድርድር ዙሪያ የአሜሪካና የዓለም ባንክ ሚና መለየት እንዳለበት ኢትዮጵያ አሳሰበች
ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ የተፋሰሱ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በማክበር የመጠቀም መብቷን አሳልፋ እንደማትሰጥ መንግስት አስታውቋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ እና ሂደት እንዲሁም የድርድር ሁኔታ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጠቅላይ ሚንስትር ፅ/ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን የምትገነባው ሙሉ መብቷ ስለሆነ እና ግድቡን መገንባት የሌላ ሀገርን ደጅ መጥናት የሚጠይቅ አለመሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስታውቀዋል፡፡
የሕዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያ የግዛት ክልል ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ በሚፈስስ ወንዝ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሃብት መሆኑንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለፁት።
ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት የማላቀቅ ሙሉ መብት አላት ያሉት አቶ ገዱ ሆኖም በዚህ ወንዝ ላይ የምትገነባው ግድብ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ተፅእኖ እንዳያሳድር በማድረግ ነው ብለዋል።
ከግድቡ ዲዛይን ጀምሮ ግንባታው ይህንን ታሳቢ በማድረግ እየተከናወነ ቢገኝም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ማረጋገጫ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ወደ ድርድር መገባቱን አቶ ገዱ ገልፀዋል።
በዚህ የድርድር ሂደትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተደራድረው ልዩነታቸውን ማጥበብ መቻላቸውን ነው ያነሱት።
ስምምነት ባልተደረሰባቸው የቴክኒክና የህግ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር በድርድር እፈታለሁ ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን እና አንዳንዶቹ ጉዳዮች ላይ ጊዜ በመውሰድ በደንብ መነጋገር እንደምትፈልግም ገልፀዋል፡፡
በድርድሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚገባ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዩን በደንብ መገንዘብና መሳተፍ አለበት፤ አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ከታዛቢነት አልፎ ህግ አርቅቆ የማቅረብ ፍላጎታቸውን አቁመው ሚናቸውን መለየት አለባቸው ሲሉም አቶ ገዱ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
ለሁሉም መፍትሄ የሚሆነው መደራደር እና በመጨረሻም ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ መሆኑን በመግለጽ ግብፅ የምታሰማው ዛቻ ጥቅም የለሽ እና ግንኙነትን ከማሻከር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ልትገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በድርድሩ ሂደት ሱዳን ግድቡ ይጠቅመኛል የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላት ያነሱት አቶ ገዱ፣ የአባይ ውሃን የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ ብቻ መሆኗን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በድርድር መርህ ላይ ተመስርታ፤ አንዳንዴም ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት የበለጠ ተጨንቃ እየሰራች መሆኑን በማንሳት ግድቡንም በዚሁ መሰረት እየገነባች ነው ብለዋል።
አሜሪካ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሀገራቱ በራሳቸው ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ግፊት በማድረግ በጎ ሚናዋን ብቻ እንድትወጣ፣ ከዚህ ያለፈ ሚና ማንንም እንደማይጠቅም እና በሌላ ተፅዕኖ የሚሆን ነገር እንደማይኖር አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ከብረት ስራ፣ ከተርባይን ተከላ እና ከተቋራጮች አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ከነበሩበት ችግሮች ወጥቶ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት።
በቻይና የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ አስፈላጊ እቃዎች በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተወሰነ እክል መፍጠሩን ያነሱት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፣ በተቻለ ፍጥነት ግን ግንባታውን በማከናወን አሁን ላይ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሀምሌ ወር ላይ ግድቡ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር በማረጋገጥም በዚህ ጊዜ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያዝ ግልፅ አድርገዋል።
ያንን ተከትሎም በየካቲት እና መጋቢት ወር አካባቢ ሙከራ እና ሀይል የማመንጨት ስራ ይጀመራል ብለዋል።
ከውሃ ሙሌትና አለቃቅ ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆኑ የህግ ማዕቀፎች እንዲቀርቡ አንፈልግም ሲሉም ተናግረዋል።
ከአሜሪካ ሚና ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባ ላይ አደራዳሪም ሆነ አመቻች እንደማትፈልግ በግልፅ አስቀምጣ የነበረ ቢሆንም፥ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጥያቄ መሰረት በታዛቢነት እንዲገቡ መደረጉን ነው ያነሱት።
በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይም አሜሪካ በዚሁ ሚናዋ ነበር የቀጠለችው ብለዋል፡፡
ምንጭ፡- ኤፍቢሲ