ምእራባውያን ሀገራት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች፣ የኢትዮጵያን ፊደል ለጹህፍ እንዳይጠቀሙ ተጽእኖ ማሳደራቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ ተናግረዋል
በዓለም ላይ ካሉት ከ5 ሺህ በላይ ቋንቋዎች አንድ ሶስተኛው በአፍሪካ እንደሚገኙ የቋንቋ አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁንና አሁን ላይ በአፍሪካ የራሷ ፊደላት ያላት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ሆናለች፡፡
እነዚህ ቋንቋዎች እንደ ሰው ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ ከዚያም በተለያዩ ምክንያቶች ይሞታሉ፡፡
በኢትዮጵያም በየጊዜው የተወለዱ፣ ያደጉ እና የሞቱ ቋንቋዎች እንዳሉ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ጥናት ያስረዳል፡፡በኢትዮጵያ ከ80 በላይ ቋንቋዎች አሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ሙልጌታ ስዩም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከኢትዮጵያ በቀር ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የራሳቸውን ፊደል ያጡት በቅኝ ገዥ ሀገራት ተጽዕኖ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ከቅኝ ግዛት ነጻነት በኋላ በኢትዮጵያ በሰብዓዊነት ድጋፍ እና በመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ምዕራባዊያን ቋንቋዎቻችንን ፊደላቸውን በላቲን እንዲቀርጹ ማድርጋቸውን ዶ/ር ሙሉጌታ ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት ከ80 በላይ ቋንቋዎች መከከል 52ቱ የራሳቸውን ፊደል ቢቀርጹም ከዚህ ውስጥ 40ዎቹ ፊደላቸውን በላቲን ፊደላት ሲቀርጹ 12ቱ ብቻ የኢትዮጵያን ፊደል ተጠቅመው የራሳቸውን ፊደል መቅረጻቸውን ዶክተር ሙልጌታ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ሙለጌታ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ፊደል የሚለባው በሂደት ከጥንት ከሳባውያን እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ንጥረ ድምጾች እየወሰደ ያደገውን የግእዝን ፊደል ነው፡፡
ይህ ድርጊት በአፍሪካ የራሷን ፊደል በመቅረጽ ብቸኛዋ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ ውርደት ነው የሚሉት ዶክተር ሙልጌታ ምዕራባዊያን ሀገራት ሳናውቀው በቁማችን ቀስ በቀስ ቅኝ እየገዙን ነው ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
ምዕራባዊያን እስከታችኛው ማህበረሰብ ድረስ በመውረድ የኢትዮጵያ ፊደል የሚጠቅመው ለሴሜቲክ ቋንቋዎች ብቻ ነው በሚል የተሳሳተ ሀሳባቸውን ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ፊደሎቻቸውን ወደ ላቲን ቋንቋ እንዲቀይሩ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን እንደቀጠሉ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ይሁንና የኢትዮጵያ ፊደላት ከላቲን ፊደላት ሲነጻጸሩ ለመማር ቀላል፣ ለመጻፍ አመቺ እና በጀት ከመቆጠብ አንጻር በእጅጉ የተሻሉ መሆናቸውን ዶክተር ሙልጌታ ተናግረዋል፡፡
የኩሸቲክ፣ የኦሞቲክ ቋንቋ ቤተሰብ የሆኑ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ፊደላቸውን በኢትዮጵያን ፊደል ተጠቅመው የቀረጹት እስካሁን ምንም አይነት ችግር እንዳልገጠማቸው በጥናት መረጋገጡን የሚናገሩት ዶክተር ሙልጌታ ግዕዝ፣ አማርኛ፣ ኩናማ፣ ባስኬቶ፣ ሳሆ፣ ሀረሪ፣ ጉራጊኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች ፊደላቸውን በኢትዮጵያ ፊደላት ከቀረጹት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አንድ ቋንቋ ፊደሉን በኢትዮጵያ ፊደላት ሲቀርጽ የቋንቋው ተናጋሪዎች የሚጽፉት እና የሚናገሩት ተመሳሳይ ይሆናል የላቲን ፊደል ግን በአናባቢዎች ወይም ቫወሎች ምክንያት የምትናገረው እና የምትጽፈው የተለያየ ይሆናልም ይህ መሆኑ ተማሪዎች በቀላሉ ቋንቋቸውን ቶሎ እንዳያውቁት ያደርጋል ሲሉ ዶክተር ሙልጌታ አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፊደላት ላቲን ፊደላት የሌሉት ብዙ ነገሮች አሉት የሚሉት ዶክተር ሙልጌታ የምዕራባዊያን ሀገራት ጥረት ኢትዮጵያዊያንን ከጋራ ታሪካቸው በመነጣጠል ለራሳቸው እንዲመች አድርገው በመስራት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የ3 ሺህ ዘመናት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ታሪኮቿ፣ ባህሏ እና ሌሎች የምርምር ስራዎቿ የተጻፉት በሀገርኛ ቋንቋዎች በመሆኑ አንድ የኢትዮጵያ ቋንቋ ፊደሉን በላቲን ቋንቋ ሲቀርጽ በዚያው ልክ ትውልዱን የራሱን ታሪክ እንዳያነብ እና እንዳያውቅ ስለሚያደርግ ከሀገሩ ጉዳዮች ማራቅም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
“ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ታሪኳም የሁላችን ነው” የሚሉት ዶክተር ሙልጌታ ኢትዮጵያዊያን ፊደላቸውን በሀገር በቀሉ ፊደል ሲቀርጹ በዛውም ሀገራዊ አንድነታችን ከመጥበቁ ባለፈ የሚያግባቡን ታሪኮች ይበዛሉ ሲሉ አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ቋንቋዎቻቸውን በኢትዮጵያ ፊደላት ካስቀረጹ እና የላቲን ቋንቋ ተጽዕኖ በዚሁ ከቀጠለ ኢትዮጵያ የራሷ ፊደል ያላት ሀገር ናት የሚለው አኩሪ ታሪካችን ተቀይሮ ሙሉ በሙሉ እንደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እጅ መስጠታችን አይቀሬ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቋንቋ ፊደላት ቀረጻ በግድ የሚሆን አለመሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ሙልጌታ ሁሉም ዜጋ እና ምሁራን ስለ ምዕራባዊያን ሴራ እንዲያውቁ በማድረግ ፊደላቸውን ወደ ሀገር በቀል ፊደላት እንዲቀርጹ ማድረግ ግን ይቻላልም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቋንቋዎች ታሪክ ጋፋት፣መስመስ እና ወይጦ የተባሉ ቋንቋዎች ሙሉ ለሙሉ የሞቱ ቋንቋዎች እንደሆኑ ዶክተር ሙልጌታ ነግረውናል፡፡
በአባይ ዳርቻ አካባቢ በሚኖሩ የጋፋት ማህበረሰብ አባላት ወደ ደቡብ ጎጃም እና ምስራቅ ወለጋ ተሰደው ቋንቋቸውን ትተው ሌላ ቋንቋ መናገር በመጀመራቸው ምክንያት ጋፋት የተባለው ቋንቋቸው ለመሞቱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
በጉራጌ ማህበረሰብ ይነገር የነበረው መስመስ ቋንቋም በጊዜ ሂደት የቋንቋው ተናጋሪዎች በመጥፋታቸው ቋንቋው መሞቱም ተገልጿል፡፡
በጣና ሀይቅ አካባቢ በሚኖሩ የወይጦ ማህበረሰብ ይነገር ነበረው ወይጦ ቋንቋም በጊዜ ሂደት አንድም ተናጋሪ ጠፍቶ ቋንቋው ሊሞት እንደቻለ ዶክተር ሙልጌታ አክለዋል፡፡
ቋንቋዎች ከስርዓተ ትምህርት ውጪ ሲሆኑ፣ ብዙሃን መገናኛዎች በየዕለቱ ስራዎቻቸው ላይ ሳይጠቀሟቸው ሲቀሩ ፣ ከአስተዳድራዊ አገልግሎት ሲወጡ እና ቀስ በቀስ ቋንቋዎች በቤተሰብ ደረጃ ብቻ ሲጠቀሟቸው ተናጋሪዎች ሲጠፉ ሊሞቱ እንደሚችሉ የተናገሩት ዶክተር ሙልጌታ በተወሰኑ ማህበረሰቦች ላይ በሚፈጸሙ ጅምላ ጭፍጨፋ፣ ጦርነት እና ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋዎች መከሰት ደግሞ ቋንቋዎች በድንገት እንዲሞቱ ያደርጋልም ብለዋል፡፡
እንዲሁም ቋንቋዎች ለተመረጡ እና ለተወሰኑ አገልግሎት ብቻ ሲዉሉ ለአብነትም ለጸሎት እና ሌሎች መሰል አገልግሎቶች ብቻ ሲጠቀሟቸው ቀስ በቀስ ሊሞቱ እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡
ከ10 ሺህ በታች ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ሁሉ የመጥፋት አደጋ እንደተደቀነበት የሚገለጽ ሲሆን በኢትዮጵያ ካሉ ከ80 በላይ ቋንቋዎች መካከል 45ቱ የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡
በደቡብ ክልል የሚገኘው ኦንጎታ አንዱ ነው፡፡ ይህ ቅንቋ በአንጻራዊነት ከሌሎች አቻ ቋንቋዎች በመጥፋት ላይ ያለ ሲሆን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ78 እስከ 100 ተናጋሪዎች እንዳሉት ዶክተር ሙልጌታ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አንፊሎ፣ ናርቦሬ፣ አርጎባ፣ አንጌ፣ ባሌ፣ ባስኬቶ፣ ባኢሶ፣ ቡዲ፣ ቡርጂ፣ ጉጂ፣ ዳሰነች፣ ጋንዛ፣ ቅማንት፣ ዲሜ፣ ሀዞ ፣ሀሮ እና ሌሎችም የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው ቋንቋዎች ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ሙልጌታ ገለጻ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የቋንቋ ፖሊሲ ዜጎች በራሳቸው ቋንቋዎች እንዲማሩ፣ እንዲጽፉ እና እንዲመራመሩ የሚያደርግ በመሆኑ ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዳይሞቱ ያደርጋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የፌደራል መንግስት ተጨማሪ የስራ ቋንቋዎችን ወደ ስራ ለማስገባት እና ክልሎች ተማሪዎች ተጨማሪ ቋንቋዎችን እንዲናገሩ በትምህርት ስርዓቶቻቸው ለማካተት እያደረጉት ያለውን ጥረት በበጎ ጎኑ አንስተዋል፡፡
በዓለም የሞቱ ቋንቋዎች ታሪክ መልሶ ወደ ህይወት የተመለሰው የእስራኤሉ እብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን ተናጋሪዎቹ በጦርነት ምክንያት ሲበታተኑ እና እስራኤላዊያን የተሰደዱበትን ቋንቋዎችን ይናገሩ ስለነበር እብራይስጥ የሞተ ቋንቋ ሆኖ ነበር፡፡
ይሁንና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እስራኤላዊያን ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ምክንያት እብራይስጥ ቋንቋን ወደ ህይወት መልሰውታል፡፡ ከዚህ ውጪ ሞቶ ወደ ህይወት የተመለሰ ቋንቋ እንዳለ መረጃ አለመኖሩ ተገልጿል፡፡