የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቻይንኛ ቋንቋን በሁለተኛ ድግሪ ማስተማር ሊጀምር ነው
በቀጣይ ሌሎች ቋንቋዎችንም በማስተርስ ማስተማር እንደሚጀመር አስታውቋል
ዩኒቨርሲቲው ቻይንኛ (መንደሪን) ቋንቋን በመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር የጀመረው ከ5 ዓመታት በፊት ነው
የቻይና (መንደሪን) ቋንቋን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ድግሪ ለማስተማር ዝግጅት መጀመሩን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተቋሙ ቻይንኛ ቋንቋን በሁለተኛ ድግሪ ለማስተማር ዝግጅት አድርጓል ብለዋል።
ትምህርቱ በ2014 ዓ.ም እንደሚጀመርም ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል። ዩኒቨርሲቲው ከአምስት ዓመታት በፊት ቻይንኛ (መንደሪን) በመጀመሪያ ድግሪ ማስተማር መጀመሩን የገለጹት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ አሁን በሁለተኛ ቋንቋ ለመስጠት ፕሮግራም ተቀርጿል ብሏል።
የቻይና ቋንቋን (መንደሪን) በሁለተኛ ድግሪ ለማስተማር የተወሰነው በርካታ ፈላጊዎች በመኖራቸው መሆኑንም ዩኒቨርሰቲው አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ብዙ ተማሪ እንደሚማር ተስፋ እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህ መርሃ ግብር ከቻይና መንግስት ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
በቀጣይ ጊዜያት ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ እና አረብኛ ለመጀመር መታቀዱን የገለጹት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ የቻይና ቋንቋን አስቀድሞ ማስተማር የተፈለገው ብዙ ተማሪዎች ፍላጎት ስላላቸው እንደሆነ ለአል ዐይን ተናግረዋል።