ፖለቲካ
ከ31 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
በፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ሳይጀመር በቆየባቸው ከፊል ስፍራዎች ምዝገባ እየተጀመረ መሆኑ ተገልጿል
በሦስት ክልሎች እስካሁን የመራጮችን ምዝገባ ማከናወን ያልተጀመረባቸው ቦታዎችም አሉ ተብሏል
የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከአንድ ወር በኋላ ለሚካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ 31 ሚሊዮን 724 ሺህ 947 መራጮች ካርድ ወስደዋል።
14 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የምርጫ ካር ድ ያወጡበት ኦሮሚያ ክልል እና 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ካርድ የወሰዱበት አማራ ክልል በአንጻራዊነት የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል ሲሉ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ ገልጸዋል።
በትናንትናው ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው የመራጮች ምዝገባ ለሁለተኛ ጊዜ እስከ ቀጣይ አርብ ድረስ መራዘሙ ይታወሳል።
እስካሁን በ43 ሺ 17 የምርጫ ጣቢያዎች ነው ከ31 ሚሊየን በላይ ዜጎች የምርጫ ካርድ መውሰዳቸው የተገለጸው፡፡
በፀጥታ ችግር ምክንያት የመራጮች ምዝገባ ሳይጀመር በቆየባቸው በኦሮሚያ ክልል በአራቱም የወለጋ ዞኖች፣ በቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ እና የአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ልዩ ዞን ምዝገባ እንዲጀመር በመደረግ ላይ መሆኑንም ቦርዱ ገልጿል።
ይሁንና አሁንም በመተከል፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሶስት የምርጫ ክልሎችና ደቡብ ክልል 2 የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ አለመጀመሩ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡