ህንድ በሀገር ውስጥ በረራዎች በርካታ ሰዎችን በማጓጓዝ ክብረወሰን ሰብረች
በሀገሪቱ በአንድ ቀን ብቻ 456 ሺህ ሰዎች የተጓጓዙባቸው የሀገር ውስጥ በረራዎች ተደርገዋል
ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኋላ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ መነቃቃት እያሳያ ነው
ህንድ በአንድ ቀን ውስጥ በርካታ መንገደኞችን በአውሮፕላን በማጓጓዝ አዲስ ክብረወሰን ይዛለች።
በሀገሪቱ 456 ሺህ ሰዎች የተጓጓዙባቸው 2 ሺህ 978 የሀገር ውስጥ በረራዎች ተደርገዋል።
ከትናንት በስቲያ የተደረጉት በረራዎች ህንድን በሀገር ውስጥ በረራ ከፍተኛ መንገደኞችን በማስተናገድ ቀዳሚዋ የአለማችን ሀገር እንድትሆን ማድረግ ችለዋል።
“የሀገር ውስጥ በረራዎች መመንደግ ከኮቪድ በኋላ የህንድ ኢኮኖሚ እያደገ መሄድን ያመላክታል” ብለዋል የህንድ የአቪየሽን ሚኒስትር ዮቲራዲትያ ሲንዲያ።
በ2023 የመጀመሪያ ሶስት ወራት 37 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች በሀገር ውስጥ በረራዎች መስተናገዳቸውን ሚኒስትሩ አንስተዋል።
ይህም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት የ51 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው።
የህንድ አየርመንገድ አውሮፕላኖች ወንበሮች በመንገደኞች የመያዝ ምጣኔያቸውም ከቻይና፣ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ አውስትራሊያ እና ብራዚል የተሻለ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
ይሁን እንጂ የአውሮፕላን ነዳጅ መወደድ እና የሩፒ ከዶላር አንጻር ምንዛሬው መውረድ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ እንዲንር በማድረግ የአየርመንገዶቹን ተወዳዳሪነት እየተፈታተነው ነው ተብሏል።
ህንድ በቀጣት አመታት ከ1 ሺህ 100 በላይ አውሮፕላኖችን ለመግዛት ስምምነት ተፈራርማለች።
ኤር ኢንዲያ ብቻ 470 አውሮፕላኖችን ከኤርባስ እና ቦይንግ ለመግዛት የደረሰው ስምምነት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ቀዳሚ ሆኖ ተጠቅሷል።
በህዝብ ብዛት የቻይናን ደረጃ የተረከበችው ህንድ በአቪየሽን ዘርፍ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደምትሆን እየተነገረ ነው።