ህንድ የፍቅረኞች ቀን “ላሞችን በማቀፍ ቀን” እንዲተካ ያሳለፈችው ውሳኔ…
ለዘመናት ላሞች እንደ ቅዱሳን በሚከበሩባት ሀገር፥ የሂንዱ የተከበረውን ባህል እንጂ የምዕራባውያንን የፍቅረኞች ቀን ማክበር አይገባም ብላለች
ነገ የሚከበረው የፍቅረኞች ቀን ላሞችን በማቀፍ ቀን እንዲለወጥ ያሳለፈችው ውሳኔም ከበርካታ ተቃውሞና ስላቅ በኋላ ተቀልብሷል
ህንድ የፍቅረኞች ቀን “ላሞችን የማቀፍ ቀን ” ሆኖ እንዲከበር ያስተላለፈችው ውሳኔ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።
ለዘመናት ላሞች እንደ ቅዱሳን በሚከበሩባትና በሚመለኩባት ሀገር፥ የምዕራባውያን የፍቅረኞች ቀን ቦታ ሊሰጠው እንደማይገባ ተገልጿል።
ነገ የሚከበረውን “የፍቅረኞች ቀን”ም “ላሞችን በማቀፍ ቀን” ለውጦ የህንዳውያንን የዘመናት ባህልና ታሪክ እና ታሪክ ማውሳት እንደሚገባ ነው የሀገሪቱ የእንሰሳት ጥበቃ ቦርድ ያስታወቀው።
የፈረንጆቹ የካቲት 14ትን “የላሞች ማቀፍ ቀን” ሆኖ እንዲከበር ውሳኔውን ሲያሳልፍም በህንድ ባህልም ሆነ በገጠር ክፍለ ኢኮኖሚ ያላቸውን ድርሻ በማንሳት ነው።
በበርካታ የህንድ ከተሞች ላሞችን መሸጥም ሆነ ማረድ የተከለከለ ተግባር ነው።
“ላሞች ለሁሉም ወገን የሚሰጡ ቸር ፍጥረት ናቸው” ያለው ተቋሙ፥ ላሞችን የማቀፍ ጥንታዊ የሂንዱ እምነት በምዕራባውያን ተጽዕኖ ስር እየወደቀ መምጣቱን ያብራራል።
በዚህም የፍቅረኞችን ቀን ከማክበር ይልቅ ከ80 በመቶ በላይ ህንዳውያን የሚከተሉትን የሂንዱ እምነት መገለጫ ማስቀጠሉ ይሻላል ብሎ ውሳኔውን ማሳለፉንም ሲ ኤን ኤን አስታውሷል።
ይህ ውሳኔ ግን በበይነ መረብ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ኋላ ላይም ውሳኔው ተቀልብሷል።
የፍቅረኞች ቀንን በላሞች ማቀፍ ቀን የመቀየሩ ውሳኔ ህንዳውያንን በሁለት ጎራ ከፍሎ መነጋገሪያ ያደረገ ብቸኛ ጉዳይ አይደለም።
በ2019 ላሞችን የሚንከባከብ ራሽትሪያ ካምዴሁ አዮግ የተሰኘ ተቋም ያቋቋመችው ህንድ፥ ብሄራዊ “የላሞች ሳይንስ” አጋዥ መጽሃፍ አውጥታ ነበር።
በዚህ መጽሃፍ ውስጥም በአንድ ጊዜ ላሞችን ማረድ የመሬት መንቀጥቀት አደጋ ያስከትላል የሚል በሳይንስ ያልተረጋገጥ ሃሳብ ተካቷል።
የህንድ ላሞች የሚሰጡት የወተት ጥራትም በአለም ላይ ተወዳዳሪ እንደሌለው ያለምንም ማረጋገጫ አስቀምጧል።
በህንድ ላሞችን የፖለቲካ መሳሪያ የማድረጉ ጉዳይም ለዘመናት ቀጥሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ አስተዳደርም ትልቁ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል።
ሞዲ በ2014ቱ የምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ላሞችን ከመታረድ የሚታደግ አቢዮት እንደሚጀምሩ መነጋራቸውም የሚታወስ ነው።
የባሃራቲያ ጃናታ ፓርቲ ሌላ ህግ አውጪም “ላሞችን እንደ እናቶቻቸው የማይመለከቱ ሰዎችን እጅና እግራቸውን እቆርጣለሁ፤ እገድላለሁ” ሲሉ መደመጣቸውን ሲ ኤን ኤን አስታውሷል።
በርካታ ህንዳውያንም ላሞችን መንከባከብና ማምለክን ባይቃወሙም፥ ለህዳጣን እምነት ተከታዮች እና ለሴቶች የሚኖረው ክብር ከላሞች ያነሰ መሆኑ ያሳስባቸዋል።