በሕንድ ባለፉት 70 ዓመታት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዜጎች ተወልደዋል
ህንድ በዓለም የህዝብ ቁጥር ቀዳሚ መሆኗ እድል ወይስ እርግማን?
ላለፉት 70 ዓመታት የዓለማችን ቀዳሚ የህዝብ ባለቤት የሆነችው ቻይና ተራዋን ለህንድ አስረክባለች።
የሕንድ የህዝብ ብዛት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን እንደደረሰ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስነ ህዝብ ፖሊሲ አስታውቋል።
አንድ ሕንዳዊ እናት በአማካኝ ሁለት ህጻናትን የመውለድ ምጣኔ ያላት ሲሆን ይህም ከ50 ዓመት በፊት ከነበረው የስድስት ልጅ ውልደት ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር በ60 በመቶ ቀንሷል ተብሏል።
ይሁንና በቻይና ተጥሎ የቆየው የአንድ ልጅ ፖሊሲ የቤጂንግን ህዝብ ቁጥር በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉ ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ የህንድ ህዝብ ቁጥር እድገት ከቻይና መብለጡ ምን ጉዳት እና እድል ይኖረዋል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል።
ሕንድ ከብሪታንያ ነጻነቷን ባገኘችበት ከ1950 ዓመት የህዝብ ብዛቷ 361 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በ70 ዓመት ውስጥ ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ዜጎች መወለዳቸው ተገልጿል።
ይህ የህዝብ ቁጥር በቀጣዮቹ 40 ዓመታት ውስጥ ተመሳሳይ እድገት ይኖረዋልም ተብሏል።
ይህ የህዝብ ቁጥር ባለቤት የሆነችው ሕንድ በየዓመቱ ሰፊ ለስራ ዝግጁ የሆነ የሰው ሀይል የሚያስገኝላት ሲሆን ይህም ለኢኮኖሚው የራሱ አቅም ይሆናል።
ከዚህ በተጨማሪም የሕንድ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖን የሚጨምር ሲሆን በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አባል የመሆን የዘመናት ጥያቄዋ እልባት ያስገኝላታልም ተብሏል።
ከዚህ በተቃራኒ ግን ለዚህ ሁሉ ህዝብ የስራ እድል መፍጠር፣ የወጣቶችን እና ሴቶችን ኑሮ ሁኔታዎችን ማሻሻል፣ መሰረተ ልማት እና አገልግሎት መስጠት ዋነኛ ፈተና ሊሆንባት ይችላልም ተብሏል።
እንዲሁም እድሜያቸው ለገፉ ሕንዳዊያን ድጋፍ እና እንክብካቤ ማድረግ ሌላኛው የህንድ ትልቁ ፈተና እንደሚሆንም ተገልጿል።