በዓለም ዙሪያ ወደ 16 ቢሊየን የሚጠጉ የሞባይል ስልኮች አሉ
ባለንበት የፈረንጆቹ 2022 ዓመት 5 ነጥብ 3 ቢሊየን ሞባይል ስልኮች እንደሚጣሉ የኤሌክትሪክ እና ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ውጋጅን አስመልክቶ የተካሄደ ፎረም አስታወቀ።
ፎረሙ በጥናት ተመለርኩዞ ባወጣው መረጃ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 16 ቢሊየን የሞባይል ስልኮች አሉ ያለ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ አንድ ሶስተኛው ምንም አይነት አግልግሎት እየሰጡ አይደለም።
ባለንበት የፈረንጆቹ 2022 ብቻም በዓለም ዙሪያ 5 ነጥብ 3 ቢሊየን የሞባይል ስልኮች በቆሻሻነት እንደሚጣሉም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሰባሰበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ አስታውቋል
ፎረሙ አክሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጣሉ ከኮምፒተር ጀምሮ እስከ ታብሌት እንዲሁም የልብስ ማጠቢያዎች፣ ቴሌሺዥኖች እንዲሁም ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ብዛት ተራራ የመፍጠር አቅም እንዳላቸው አስታውቋል
እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ የሚወገዱ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች መጠን 74 ሚሊየን ቶን እንደሚደርስም ፎረሙ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።
አሁን ባለንበት የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ሮያል የኬሚስትሪ ማህበረሰብ የሚጣሉ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን አስመልክቶ አዲስ ቅስቀሳ የጀመረ ሲሆን፣ ይህም መገልገያዎቹ ዳግም ለሌላ ምርት እንዲውሉ የሚያስችል ነው ተብሏል።
በሚጣሉ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ውስጥ በርካታ ጠቃሚ ቁሳቁሶች አሉ የተባለ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ እና የሶላር ፓኔሎችን ጨምሮ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ለመስራት የሚያስችሉ ቁሶች እንደሚገኝባቸውም ተነግሯል።
አሁን ባለው መረጃ መሰረት በዓለማችን ላይ የአገልግሎት ዘመናቸውን ከጨረሱ የኤሌክትሪክ እና የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዊች ውስጥ ለዳግም ምርት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት 17 በመቶው ብቻ ነው።
በተባበሩት መንንግስታት ድርጅን ዓለም አቀፉ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ህብረት ይህንን መጠን በቀጣዩ ዓመት ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ እቅድ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።