ሃራልድ በወረርሽኙ ምክንያት በአካል የማያገኟቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ሲሉ በ83 ዓመታቸው ሞባይል ስልክ መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል
የኖርዌዩ ንጉስ ሃራልድ የእጅ ስልክ ለመጀመሪያ ጊዜ መጠቀም የጀመሩት 83ኛ የልደት በዓላቸውን ካከበሩበት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ነው፡፡
ሃራልድ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በአካል የማያገኟቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ሲሉ ሞባይል ስልክ መጠቀም መጀመራቸውን ከሰሞኑ ኦስሎ በሚገኘው ቤተመንግስታቸው ለሃገሪቱ የፓርላማ አባላት ግብር በጣሉ (የራት ግብዣ) ጊዜ ተናግረዋል፡፡
ንጉሱ ሞባይል ስልክ ለመጠቀም 40 ዓመት ወስዶብኛል ሲሉ ነው ለግብር እድምተኞቻቸው የተናገሩት፡፡ ይህም እድምተኛውን ያዝናና ነበር እንደ ሃገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘገባ፡፡
“ከባለፈው መጋቢት ወዲህ የተማርነው ነገር ቢኖር እርስ በእርስ ለመገናኘት ያስቻለንን የቴክኖሎጂን ጠቃሚነት ነው፡፡ ሞባይል መጠቀም የጀመርኩ ጊዜ ቤተሰቤ ተደስቶ ነበር፡፡ ይህ እንዲሆን 40 ዓመታት ብቻ ነው የፈጀብኝ” ብለዋል ንጉስ ሃራልድ፡፡
የ84 ዓመቷ ባለቤታቸው ንግስት ሶንጃ ግን ከንጉሱ በተሻለ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የአፕል ሰዓቶችን ጨምሮ ታብሌት ኮምፒውተሮችን ይጠቀማሉ፡፡
ከፈረንጆቹ 1991 ጀምሮ ኖርዌይን በንግስና እየመሩ ያሉት ሃራልድ ከንግስት ሶንጃ ጋር 53 የጋብቻ ዓመታትን አሳልፈዋል፡፡
ልዑል አልጋወራሽ ሃኩን እና ልዕልት ማርታ ሉይዜ የተባሉ ሁለት ልጆች እንዳሏቸውም ነው የኢንሳይደር ዘገባ የሚያመለክተው፡፡