ቺካጎ፣ ፓሪስ፣ ቦስተን እና ኒውዮርክ እስከ 5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል
በፈረንጆቹ 2022 ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የተየባቸው ከተሞች ዝርዝር ይፋ ሆኗል።
ግሎባል ትራፊክ ስኮርካርድ ባደረገው ጥናት መሰረት፥ የአሜሪካ ግዙፍ ከተሞች አሁንም ረጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች የሚታዩባቸው ሆነዋል።
ከአለማችን አምስቱ ከፍተኛ መጨናነቅ የሚታይባቸው ናቸው ተብለው የተለዩ ከተሞችን ታይምስ አውት የተሰኘው በጉዞና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ መጽሄት ይዞ ወጥቷል።
1. ለንደን
የእንግሊዟ መዲና ጎዳናዎች በተሽከርካሪዎች በመጨናነቅ ቀዳሚውን ስፍራ ያዛለች።
በፈረንጆቹ 2022 በከተማዋ በአማካይ 156 ስአታት በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ይባክናሉ ነው የሚለው ጥናቱ።
ይህም በ2021 ከነበረው የ5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተነግሯል።
2. ቺካጎ
የአሜሪካዋ ቺካጎ ከተማ ደግሞ ከለንደን በመቀጠል ስአታትን በመንገድ ላይ ማሳለፍን የምታስገድድ ከተማ ሆናለች። በቺካጎ በ12 ወራት ውስጥ 155 ስአታት በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ይባክኑ ዘንድ ግድ ሆኗል ነው ያለው ግሎባል ትራፊክ ስኮርካርድ በጥናቱ።
3. ፓሪስ
የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ አሽከርካሪዎች ረጅም ስአት መንገድ ላይ የሚያጠፉባት ሶስተኛዋ የአለማችን ከተማ ተብላለች። በፓሪስ በ2022 አሽከርካሪዎች በአማካይ 138 ስአታትን መንገድ ላይ አጥፍተዋል። ይህም ከ2021 የ1 በመቶም ቢሆን መቀነሱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ፓሪስን ከአለማችን የተጨናነቁ ከተማ ከመሆን አልታደጋትም።
4. ቦስተን
የአሜሪካዋ ቦስተን ከፍተኛ መጨናነቅ ከታየባቸው ከተሞች ውስጥ አራተኛውን ደረጃ ይዛለች። ቦስተን በመንገዶች መዘጋጋት ምክንያት አሽከርካሪዎች በአመት 134 ስአታትን ለማባከን የሚገደዱባት ከተማ መሆኗንም ጥናቱ ታሳያል። በ2022 የተመዘገበው ውጤት ከ2021 በ72 በመቶ መጨመሩም የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየወደቀ መምጣት ያሳያል ተብሏል።
5. ኒውዮርክ
ግዙፏ የአሜሪካ ከተማ ኒውዮርክም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከታየባቸው ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች። በኒውዮርክ ጎዳናዎች የተፈጠረው መጨናነቅ በ2022 ብቻ አሽከርካሪዎች በአማካይ 117 ስአታትን ቆመው እንዲያሳልፉ አስገድዷል። በ2021 ከነበረው መጨናነቅ በ15 በመቶ ጭማሪ የታየባት ከተማ ለአመታት ከዚህ ፈታኝ ችግሯ መላቀቅ አልቻለችም።
ግሎባል ትራፊክ ስኮርካርድ ይፋ ባደረገው ጥናት መሰረት፥ ቦጎታ፣ ቶሮንቶ፣ ፊላደልፊያ፣ ሚያሚ እና ፓሌርሞ ከ6ኛ እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።