በዓለማችን በየ24 ሰከንድ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ህይወቱን እያጣ መሆኑ ተገለጸ
የዓለም ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን በመከበር ላይ ይገኛል
በዓለማችን ከሚከሰቱ የትራፊክ አደጋ አደጋዎች 90 በመቶው ባላደጉ ሀገራት ይከሰታል
በዓለማችን በየ24 ሰከንድ አንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ህይወቱን እያጣ መሆኑ ተገለጸ።
የመንግስታቱ ድርጅት የትራፊክ አደጋን በሚመለከት ከድርጅቱ አባል አገራት ጋር በኒዮርክ መክሯል።
በዚህ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዳሉት በዓለማችን በየ24 ሰከንዱ እንድ ሰው በትራፊክ አደጋ ህይወቱን እንደሚያጣ ገለጸዋል።
በዚህም መሰረት በየዓመቱ ሚሊዮን ዜጎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እያጡ ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው አደጋውን መቀነስ የግድ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።
እንደ ዋና ጸሃፊው ገለጻ በትራፊክ አደጋ ወጣቶች፣እግረኞች እና አካል ጉዳተኞች የከፋ ተጋላጭ የሆኑ ሲሆን እነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ለሞት እና አካል ጉዳት በመጋለጣቸው በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው።
በዓለማችን በትራፊክ አደጋ በሚደርሱ ከሚሞቱ እና አካላቸው ከሚጎድሉ ሰዎች መካከል 90 በመቶው ባላደጉ አገራት እንደሚከሰትም የተመድ ሪፖርት ያሳያል።
በመሆኑም የተመድ አባል አገራትን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት የትራፊክ አደጋን መቀነስ የሚያስችሉ ስራዎችን እንዲያከናውኑ ዋና ጸሃፊው አሳስበዋል።
የዓለም ጠራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን ከፈረንጆቹ 2005 ዓመት አንስቶ በየዓመቱ ህዳር ወር ሶስተኛ እሁድ ዕለት በተለያ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል።