በ2024 ለገበያ የሚቀርቡ አይነግቡ ተሽከርካሪዎች
የጀርመኖቹ ቮልስዋገን እና መርሰዲስን ጨምሮ ታዋቂ ተሸከርካሪ አምራቾች በ2024 አዳዲስ ምርቶቻቸውን ያቀርባሉ
250 ሺህ ዶላር የሚያወጣው “አስቶን ማርቲን ዲቢ12” ከሚጠበቁት ተሽከርካሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት ይጠቀሳል
አዲስ መኪና ለመግዛት ለሚፈልጉ ሰዎች 2024 በርካታ አማራጮችን ይዞ ይመጣል።
ታዋቂ ተሽከርካሪ አምራች ድርጅቶች በሞዴልም ሆነ በፍጥነታቸው የተሻሻሉ እና በአይነታቸው ልዩ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል ተብሏል።
ቀጥሎ በ2024 ለገበያ ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁት ዘመናዊና ፈጣን ተሽከርካሪዎች ውስጥ የተመረጡ አምስት ሞዴሎችን እንመለከታለን፦
1. ዶጅ ቻርጀር ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ
የአሜሪካው ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ዶጅ የመጀመሪያውን በኤሌክትሪክ የሚሰራ መኪናውን ከወራት በኋላ ለገበያ ያቀርባል። በዘመናዊ መኪናዎቹ የሚታወቀው ዶጅ አዲሱ ምርቱን እስከ 50 ሺህ ዶላር በሚያወጣ ዋጋ ለገበያ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
2. ቮልስዋገን አይዲ በዝ
በሶስት ረድፍ ሰባት ሰዎችን እንዲይዝ ተደርጎ የተሰራው ቮልስዋገን አይዲ በዝ በ2024 ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብለው ከሚጠበቁ አይነግቡ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ይመደባል። የጀርመኑ ተሽከርካሪ አምራች ኩባንያ ይህን መኪና እስከ 58 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ሊያወጣለት እንደሚችል ቢገለጽም እስካሁን የመጨረሻ ዋጋው አልታወቀም። በኤሌክትሪክ የሚሰራው ቮልስዋገን አይዲ በዝ በአሜሪካ ግን ከ2025 በፊት ለገበያ ላይቀርብ እንደሚችል ተነግሯል።
3. ኒሳን ዜድ ኒስሞ
የውድድር መኪናዎችን በማምረት የረጅም አመታት ልምድ ያካበተው የጃፓኑ ኩባንያ ኒሳን በ2024 አዲስና ዘመናዊ ተሽከርካሪውን ለገበያ ያቀርባል። 60 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል የተባለው ኒሳን ዜድ ኒስሞ በስአት 259 ኪሎሜትር ይምዘገዘጋል። ተሽከርካሪው ከጉልበቱ ባሻገር አይን የሚስብ እንዲሆንም ተደክሞበታል ነው ያለው ኒሳን ኩባንያ።
4. መርሰዲስ ኤኤምጂ ሲ63
ሌላኛው የጀርመን ታዋቂ የመኪና አምራች ኩባንያ መርሰዲስ ቤንዝም በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ የሚሰራ “መርሰዲስ ኤኤምጂ ሲ63” የተሰኘ ምርቱን በ2024 ለሽያጭ ያቀርባል። ለሞተር የፈረስ ጉልበት በልዩ ትኩረት የተሰራበት ይህ የተሽከርካሪ ሞዴል ከ95 ሺህ ዶላር የማያንስ ዋጋ ይኖረዋል ተብሏል።
5. አስቶን ማርቲን ዲቢ12
ውበትን ከጉልበት አጣምሮ የያዘው “አስቶን ማርቲን ዲቢ12” በቀጣዩ የፈረንጆቹ አመት ለገበያ ይቀርባሉ ከተባሉት አይነግቡ ተሽከርካሪዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ተሽከርካሪው በስአት 325 ኪሎሜትሮችን መጓዝ ይችላል መባሉም ተመራጭ ያደርገዋል። አሳሳቢው ነገር የዋጋው ጉዳይ ነው፤ ከ248 ሺህ ዶላር በላይ ያስወጣልና።