የዚህ መኪና ዋጋ በኢትዮጵያ ከ1 ሺህ 500 በላይ መካከለኛ ዋጋ ያላቸው ተሽከርካሪዎች መግዛት ያስችላል
በ1939 በጣሊያኗ ማራኔሎ ምስረታውን ያደረገው ፌራሪ ውድ የሆኑ የውድድር ተሽርካሪዎችን በማምረት ይታወቃል።
በ2022 ከ5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ያስገባው ፌራሪ በየአመቱ ትርፋማነቱ እያደገ ነው።
ምንም እንኳን የመኪኖቹ ዋጋ የማይቀመስ አይነት ቢሆንም ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን መግዛት የሚያስደስታቸው ሰዎች ቀዳሚ ምርጫ ካደረጉት አመታት ተቆጥረዋል።
“ፌራሪ 250 ጂቲኦ”
በኢንዞ ፌራሪ የተቋቋመው ፌራሪ ኩባንያ ከፈረንጆቹ 1962 እስከ 1964 ድረስ 36 “ፌራሪ 250 ጂቲኦ” የሚል ስያሜ የሰጣቸውን ተሽከርካሪዎች አምርቷል።
ፌራሪ 250 ጂቲኦ ባለ 12 ሲሊንደር ሞተር ያለው ሲሆን፥ በስአት እስከ 300 ኪሎሜትር ይምዘገዘጋል።
ይህ መኪና ከቆመበት በስድስት ሰከንድ ውስጥ ፍጥነቱን በስአት 100 ኪሎሜትር ማድረስም ይችላል።
ከ1962 እስከ 1964 የተመረቱትን እነዚህን ውድ ተሽከርካሪዎች ቢሊየነሮች፣ ታዋቂ ሙዚቀኞች እና የፊልም ባለሙያዎች ሲያሽከርክሩት ይታያል።
ከፌራሪ ተሽከርካሪዎቹን ገዝተው ከአመታት በኋላ በጨረታ በውድ ዋጋ የመሸጣቸው ጉዳይም የጣሊያኑ ኩባንያ ከ60 አመት በፊት ያስተዋወቃቸው ፈጣን ተሽከርካሪዎች አሁንም ተፈላጊነታቸው መጨመሩን ያሳያል።
ከፋብሪካው ከ5 ሺህ እስከ 18 ሺህ ዶላር ሲሸጥ የነበረው ፌራሪ 250 ጂቲኦ በ2018 በጨረታ 70 ሚሊየን ዶላር መሸጡን የብሉምበርግ ዘገባ ያወሳል።
አሜሪካዊው ቢሊየነር (የዌዘርቴክ መስራች) ዴቪድ ማክኔል በጨረታ በእጁ ያስገባው የፌራሪ መኪና የአለማችን ውዱ ተሽከርካሪ ተብሎ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍሯል።
ቢሊየነሩ የፌራሪ መኪናን የገዛበት ዋጋ በኢትዮጵያ ብር ብንመነዝረው ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ይሆናል፤ ማክኔል በኢትዮጵያ መካከለኛ ዋጋ ያላቸውን 1 ሺህ 500 መኪኖች መግዛት የሚችልበትን ዶላር ፌራሪ 250 ጂቲኦ ላይ አፍስሷል።
ግለሰቡ በቀጣይ በምን ያህል ዋጋ ይሸጠዋል የሚለውም ተጠባቂ ነው።